“ዓመቱ ለእኔ እጅግ ደስ የሚል ነበር” ሎዛ አበራ

ለተከታታይ ሁለተኛ በድምሩ ለስድስተኛ ጊዜ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀችው እና ከንግድ ባንክ ጋር ተከታታይ የሊጉን ዋንጫ ያነሳችው አጥቂዋ ሎዛ አበራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ2004 ጅምሩን ቢያደርግም ከሊጉ ጋር ትውውቅ የጀመረችው 2005 ለሀዋሳ ከተማ በመጫወት ነበር፡፡ ቀስ በቀስ በምታሳየው አስደናቂ አቅም በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙ ሴት ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት መቀመጥም ችላለች። አጥቂዋ ሎዛ አበራ ከሀዋሳ በመቀጠል በደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እና በመሀል ወደ ማልታ አምርታ (ለቢርኪርካራ) በመጫወት ስኬታማ ጉዞን ማድረግ የቻለች ሲሆን በ2013 የውድድር ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሳ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመረፈረም በመጣችበት ዓመት ከክለቡ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቷ በዘለለ በግሏ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን መጎናፀፍ ችላለች። በሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያው ውድድር ላይም ቡድኗ ሁለተኛ ሆኖ እንዲጨርስ ጥራ ውድድሩን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት መፈፀም ችላለች።

ዘንድሮ በድጋሚ ከክለቧ ንግድ ባንክ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቷ በተጨማሪ በ2008 (በ57) ጎል ካጠናቀቀችበት ዓመት በኋላ (በ34) ጎሎች ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆና የፈፀመችው ሎዛ አበራ ስለ ውድድር ዓመቱ እና ስለ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቷ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርጋለች፡፡

ስለ ውድድር አመቱ…

“ዓመቱ ለእኔ እጅግ ደስ የሚል ነው፡፡ ብዙ ተደራራቢ ድሎችን እና ስኬቶችን ያሳካሁበት ዓመት ነው ፤ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡”

ለስድስተኛ ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ስለመሆኗ…

“ዋንጫን ማግኘቴም ሆነ የኮከብ ጎል አግቢነቱም ስድስት ስድስት ጊዜ ያገኘሁት በደደቢት ፣ አዳማ እና ንግድ ባንክ ነው፡፡ ለእኔ ይሄ ዓመት ቆንጆ ዓመት ነበረ። እንደ ቡድንም እንደ ንግድ ባንክ አምስት ጊዜ ያሸነፍንበት እና ሪከርድ የሰበርንበት ነው። ከዚህ በፊት ደደቢት እና ንግድ ባንክ እኩል እኩል ነበር አራት አራት ጊዜ ዋንጫ ያገኙት ፤ አሁን አምስት አድርገነው ሪከርድ ሰብረናል። ሌላው ደግሞ እኔም ኮከብ ጎል አግቢነቱን ከአምናው በተሻለ መርቻለው። በ2008 57 ጎሎችን አስቆጥሬ ነበር ፤ በዚህኛው ዓመት ደግሞ የተሻለ አስቆጥሪያለሁ። ይሄ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በየዓመቱ ራሴን እያሻሻልኩ የመጣሁበት ነው ብዬ አስባለሁ። በተቻለኝ መጠን እኔም ቡድኑም በጥሩ መንፈስ በተለይ አሠልጣኞቻችን በሚሰጡን ዲሲፕሊን እና የስልጠና መንገድ አንድ ላይ ሆነን በጣም ጥሩውን ዓመት አሳልፋፈናል።”

ባለፈውም ዓመት ዘንድሮም በተመሳሳይ ክለባችሁም ሆነ አንቺም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆናችሁ የጨረሳችውበት ሚስጥር…

“ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው ብዙ አዳዲስ የመጡ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ከእነርሱ ጋር አንድ ላይ በመሆን ከፍተኛ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ አሰልጣኛችንም እኛም ከመጀመሪያው ጀምሮ ቻምፒዮን ለመሆን ብዙ ስንጥር እና ስንደክም ነበር፡፡ ትልቁ ነገር አንድነታችን ነው ብዬ አስባለሁ አሰልጣኛኞቻችን ከሚሰጡን ስልጠና ፣ የስነ ልቦና ስራዎች ውጪ እርስ በእርስ ያለን መከባበር በተለይ ለአሸናፊነት ያለን መነሳሳት ትልቅ ነበር። አቻ ስንወጣ እንደ ሽንፈት ነው የምንቆጥረው። ውጤቶችን ይዘን ለመውጣት በጣም በብዙ ስንሰራ ነበር፡፡ ትልቁ ሚስጥር አንድ መንፈስ እና ስህተቶቻችንን ቶሎ ቶሎ ተነጋግረን ወደ ስራ መግባታችን እንዲሁም እግር ኳስን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ እንድንጫወት ፣ እንድንሰራ አሰልጣኞቻችን የሚያደርጉት መንገድ ነው ብዬ አስባለው።”

ስለ ቀጣዩ የሴካፋ የክለቦች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር…

“አምና ለዋንጫ ደርሰን ሁለተኛ ሆነን መጥተናል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ሻምፒዮን እንሆናለን ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም ልምዱን በተወሰነ መልኩ አግኝተናል፡፡ ሲቀጥል አሁን ማች ፊትነሳችንም ጥሩ ነው። በአሸናፊነት ነው እየሄድን ያለነው። እንደ አምና ዝግጅትን ብቻ አይደለም አሳልፈን የምንሄደው ፤ ከጨዋታ ላይ ተነስተን እየሄድን ስለሆነ ጥሩ ስነ ልቦና ላይ ነው የምንሆነው ብዬ አስባለሁ። ግን አሁንም ቢሆን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። አሁን እዛ ስንሄድ ከፍተኛ የሆነ ፈተና ነው የሚጠብቀን። አዲስ አየር፣ አዳዲስ ክለቦች እንዲሁም አዲስ ተጫዋቾች። ለእዚህም በዕለት ፐርፎርማንስ ላይ ከፍተኛ የሆኑ ስራዎችን ሰርተን ሻምፒዮና ሆነን ለመምጣት ከእግዚአብሔር በታች እናስባለን፡፡”