ባህር ዳር ከተማ ከመስመር ተጫዋቹ ጋር በስምምነት ተለያይቷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከጣና ሞገዶቹ ጋር ያሳለፈው ተመስገን ደረሰ በስምምነት ከክለቡ ጋር መለያየቱ ታውቋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 12ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ የቀጣይ ዓመት ስብስቡን እንደ አዲስ እያዋቀረ ይገኛል። እስካሁንም ስምንት አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከመስመር አጥቂው ተመስገን ደረሰ ጋር በስምምነት መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ የመስመር እና የፊት አጥቂው ተመስገን ካቻምና ቡድኑ ጅማ አባጅፋር በሊጉ ደካማ የውድድር አመትን ቢያሳልፍም በግሉ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተከትሎ የጣና ሞገዶቹን በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም በታሰበው መልኩ በክለቡ ግልጋሎት ሳይሰጥ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተገልጿል።

ተጫዋቹ በቅርቡም ወደ ሌላ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ለማምራት ንግግር ላይ እንዳለም የዝግጅት ክፍላችን ለማወቅ ችላለች።