ዜና ዕረፍት | የቀድሞው ተጫዋች ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ ያለፈው የቀድሞ ተጫዋች ዮናስ እንግዳወርቅ በዛሬው ዕለት የቀብር ስነ ስርዐቱ ተፈፅሟል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ መድን ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና ደደቢት በመስመር አጥቂ ስፍራ ተጫዋችነት የሚታወቀው ዮናስ እንግዳወርቅ ያለፉትን ዓመታት በጉዳት ከእግር ኳሱ ዓለም ተገልሎ የነበረ ሲሆን በድጋሚ ወደ ነበረበት የእግር ኳስ ህይወት ለመመለስ በጥረት ላይ እንደነበር አውቀናል፡፡

ባለ ትዳር እና የሁለት ሴት ልጆች አባት የነበረው ይህ ተጫዋች ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት ላይ በግል መኪናው ወደ መኖሪያ ቤቱ በማምራት ላይ ሳለ ከባቡር መስመር ጋር ተጋጭቶ ህይወቱ እንዳለፈ ለማወቅ ችለናል፡፡ በዛሬው ዕለትም የተጫዋቹ ስርአተ ቀብር በካራ መድሀኒዓለም ቤተክርስቲያን ቀትር 6፡00 ገደማ ተፈፅሟል።

ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ትመኛለች፡፡