አርባምንጭ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪው አርባምንጭ ከተማ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ነባሮችንም ውል አድሷል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ተጠናክሮ ለመገኘት አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ይገኛል፡፡ አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ማስፈረሙን እና የሁለት ነባሮችን ኮንትራት ማደሱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ኃይለማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ተመስገን ደረሰ የአዞዎቹ አዲሱ ተጫዋች ሆኗል፡፡ የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ እና የጅማ አባጅፋር የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ጥሩ የውድድር ዓመትን ካሳለፈበት አባጅፋር ወደ ባህርዳር ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አምርቶ መጫወት የቻለ ሲሆን ከሰሞኑ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው በስምምነት ከተለያየ በኋላ በአንድ ዓመት ኮንትራት ወደ ደቡቡ ክለብ ተጉዟል፡፡

ሌላኛው አዲሱ ተጫዋች አካሉ አትሞ ነው፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በጅማ አባጅፋር መለያ የተመለከትነው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ስድሰተኛ የአዞዎቹ ፈራሚ በመሆን በሁለት ዓመት ውል አርባምንጭ ደርሷል፡፡

ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የመስመር ተከላካዩ ሙና በቀለ እና የመስመር አጥቂውን ሱራፌል ዳንኤል ውልም ለተጨማሪ አንድ ዓመት አድሷል፡፡