ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ሶርያ ክለብ አምርቷል

በተጠናቀቀው ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር ቆይታ የነበረው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ሶርያ ማምራቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ስኬታማ መሆን ከቻሉ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ነው፡፡ በ2010 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቱ ባለፈ ዓመቱን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀው ግዙፉ አጥቂ በመቀጠል ወደ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም ወደ ግብፁ ኢስማኤልያ ያመራ ሲሆን በ2013 የውድድር ዘመን የመጨረሻውን ስድስት ወራት ደግሞ በሲዳማ ቡና አሳልፏል፡፡

የተጠናቀቀውን የ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከፋሲል ከነማ ጋር ዓመቱን ያሳለፈው ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ሊግ ዳግም ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ኤዥያ አምርቶ የሶርያ አንጋፋ ክለብ የሆነው አል ኢትሀድ – ኢሊፖን በይፋ መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቹ ኢትዮጵያዊው ወኪል ኤዶሚያስ በቀለ አረጋግጣለች፡፡

ክለቡ በሶርያ ሊግ ስድስት ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮን እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡