ሀዋሳ ከተማ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ ከክለቡ የታዳጊ ቡድን የተገኙትን ሦስት ተጫዋቾች ውልን አድሷል፡፡

ካለፉት ዘመናት በተለየ መልኩ በዝውውር ገበያው በንቃት በመሳተፍ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ ማድረግ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ከክለቡ የታኛው ቡድን ተገኝተው ውላቸው የተጠናቀቁ ሦስት ወጣት ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አድሷል፡፡

ቸርነት አውሽ ውሉ ለተጨማሪ ዓመት ታድሶለታል፡፡ በሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የተገኘው እና በዋናው ቡድን አምስት ዓመታትን ቆይታ ያደረገው አጥቂው በቡድኑ ተጨማሪ ሁለት ዓመት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል፡፡

ዳዊት ታደሰም ሌላኛው ውሉ የታደሰለት ተጫዋች ነው፡፡ በተመሳሳይ በሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ፍሬ የሆነው ይህ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ለሁለት ዓመታት በልጅነት ክለቡ ይቀጥላል፡፡

ሦስተኛው እና በክለቡ ውሉ የታደሰለት ተስፈኛው አጥቂ ሀብታሙ መኮንን ነው፡፡ በክለቡ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ የተሳኩ ዓመታትን ያሳለፈው እና ያለፉትን ሦስት ዓመታት በዋናው ቡድን በማደግ እየተጫወተ የሰነበተው ተጫዋቹ ውሉ መገባደዱን ተከትሎ ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን በክለቡ መዝለቁ ዕርግጥ ሆኗል፡፡