ለገጣፎ ለገዳዲ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ የሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር አገባዷል።

በ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲ የአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመን ውል ከማራዘሙ በፊት በተጫዋቾች ዝውውሩ ላይ አስቀድሞ እየተካፈለ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ አካቷል፡፡

አጥቂው ምትኩ ጌታቸው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነው፡፡ በከፍተኛ ሊግ በቡታጅራ ከተማ እና በዲላ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው ምትኩ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ወደ ቀድሞው ክለቡ አርሲ ነገሌ ተመልሶ በክለቡ ውስጥ መቆየት ችሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ ለገጣፎ ለገዳዲ አምርቷል፡፡

ሌላኛው አዲስ ፈራሚ ታዬ ጋሻው ሆኗል፡፡ ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን የተገኘው እና በአርሲ ነገሌ ላለፉት ዓመታት ሲጫወት የነበረው ወጣቱ ተከላካይ መዳረሻው ለገጣፎ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

መሐመድ ሻፊ የክለቡ ሌላኛው አዲሱ ተጫዋች ነው፡፡ በወልቂጤ ከተማ ከዚህ በፊት በተከላካይ ቦታ ላይ ሲጫወት የምናውቀው ተጫዋቹ የቡድኑ ሌላኛው አዲስ ፈራሚ ነው፡፡