ዑመድ ኡኩሪ ስለ ኦማን ጉዞው ይናገራል

በሀገራችን እና በግብፅ ሊግ ለተለያዩ ክለቦች ሲጫወት የምናቀው ዑመድ ኡኩሪ ወደ ኦማን ያደረገውን ዝውውር አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ዑመድ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን በመከላከያ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ የእግርኳስ ዘመናት አሳልፎ በ2007 ወደ ግብፅ ሊግ አምርቶ አል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያን፣ ኢ ኢን ፒ ፒ አይ፣ ኤል-ኤንታግ አል-አርቢ፣ ስሞሀ እና አስዋን ሲጫወት ቆይቶ ወደ ሀገሩ በመመለስ ካሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ለሀዲያ ሆሳዕና ሲጫወት ቆይቷል።

ከትናንት በስትያ ላይ ባስነበብናቹ ዜና ዑመድ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኤዥያ በማቅናት ለኦማኑ አል-ሱዋይክ ክለብ በአንድ ዓመት ውል መቀላቀል መቻሉን ገልፀን ነበር። ተጫዋቹም የዝውውር ሂደቱን፣ በሊጉ ስለሚኖረው ቆይታ እና በቀጣይ በሊጉ ስለሚያቅደው ነገር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

“ በግብፅ ሊግ በነበረኝ ቆይታ ይከታተሉ የነበሩ ወኪሎች ናቸው የኦማኑን የዝውውር ሂደት ያመቻቹልኝ ፤ ግብፅ መጫወት በመላው ዐረብ ሀገራት የመታወቅ ዕድሉ ሰፊ ነው። ንግግር የጀመርኩት የኛ ሀገር ሊግ ወደ መጠናቀቂያው አካባቢ ነበር። ወደ እዚህ ከመጣሁ በኋላ አስቀድሜ ስምምነት ፈፅሜ ስለነበር ወድያውኑ ፊርማዬን በማኖር ለአንድ አመት ለመጫወት ፊርማዬን አኑሬያለው። 

“በኤዥያ ክለብ ወጥቼ ስጫወት ይህ የመጀመርያዬ ነው። ከዚህ በፊት ወደዚህ አሁጉር መጥቼ ተጫውቼ አላቅም። ፈታኝ ቢሆንም መቼም በግብፅ ሊግ ተጫውቼ እዚህ ይከብደኛል ብዬ አላስብም። ከአዲሱ ቡድኔ ጋር ዝግጅት ማድረግ ከጀመርኩ አስራ ሁለተኛ ቀን ይሆነኛል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ውድድሩ ይጀምራል። እዚህ ከመጣው ጀምሮ ባየሁት ነገር በብዙ ነገር የተሻለ ነው ፤ በጣምም ደስተኛ ነኝ። ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ጊዜን አሳልፋለው ብዬ አስባለው።”