ኢትዮጵያ መድን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ነገ ይጀምራል

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መመለስ የቻለው ኢትዮጵያ መድን በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ነገ ይጀምራል።

ከከፍተኛ ሊጉ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን ከአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ጋር እንደማይቀጥል ከታወቀ በኋላ ከሲዳማ ቡና ጋር የተለያዩት ነገርግን የወረቀት ጉዳዮች ያልተገባደደላቸውን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በይፋ መቅጠር ባይችልም በአሰልጣኙ መሪነት እስከ አሁን አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ የተቀላቀለ ሲሆን ከስምንት በላይ ውላቸው የተጠናቀቁ ነባር ተጫዋቾችንም ቆይታ አሯዝሟል።

አቡበከር ኑራ ፣ ፀጋሰው ድማሙ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ሳሙኤል ዮሃንስ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ብሩክ ሙሉጌታ ፣ ሀቢብ ከማል እና ቴዎድሮስ በቀለን በአዲስ መልክ ማምጣት የቻለው ቡድኑ ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እንደሚቀላቅል የሚጠበቅ ሲሆን በአዲሱ አሰልጣኝ መሪነት የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የት እና መቼ እንደሚጀምር ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ መረጃ አግኝታለች፡፡

በዚህም ክለቡ በአዳማ ከተማ በመክተም ከነገ ነሐሴ 5 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር አውቀናል፡፡