ሱራፌል ዳኛቸው ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ሆነ

ከቀናት በኋላ የቻን የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ መርሐ-ግብር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አማካዩን ከስብስቡ ውጪ አድርጎ በምትኩ ለአንድ ተጫዋች ጥሪ አቅርቧል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደቡብ ሱዳን አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት ረቶ በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳ ጋር ለመፋለም ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል። ቡድኑ በዛሬው ዕለት የተሰባሰበ ሲሆን በጁፒተር ሆቴል ማረፊያውን እንዳደረገም ታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ቡድኑ በዛሬው ዕለት ተሰባስቦ የጂምናዚየም ልምምድ ማድረግ የጀመረ ሲሆን ወሳኝ አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸውን ግን በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ አድርጓል። በምትኩም የሀዋሳ ከተማው ወንድማገኝ ኃይሉ ጥሪ እንደተደረገበት ተገልጿል። ሱራፌል ከደቡብ ሱዳን በተደረገው የመልስ ጨዋታ ላይ በጉዳት በከነዓን ማርክነህ ተቀይሮ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ረፋድ ወደ አዳማ በማቅናት መደበኛ ልምምዱን የሚከውን ሲሆን ከሰዓትም የመጀመሪያ የሜዳ ላይ ልምምዱን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ማድረግ ይጀምራል።