የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚደረግበት ቦታ ታውቋል

ባለንበት ወር መጨረሻ በቻን የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የሚገናኙት ኢትዮጰያ እና ሩዋንዳ የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን የት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየት በየቀጠናው የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በመጀመሪያው ዙር የደቡብ ሱዳን አቻውን በደርሶ መልስ የሰፋ ውጤት አሸንፎ ወደ ዋናው ውድድር ለማለፍ ከሩዋንዳ ጋር የ180 ደቂቃዎች ፍልሚያ ብቻ ይቀሩታል። ለዚህ ወሳኝ ጨዋታ በትናንትናው ዕለት የተሰባሰበው ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ወደ አዳማ በማቅናት መደበኛ ልምምዱን እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በሀገራቸው የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም አለመኖራቸውን ተከትሎ እገዳ ላይ ቢገኙም ሩዋንዳ ከሦስት ቀናት በፊት ሜዳዋ እንደተፈቀደላት ለማወቅ ተችሏል። ይህንን ተከትሎ ሩዋንዳ ነሐሴ 29 የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ በሁዬ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደምታስተናግድ ይፋ ተደርጓል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ግን አሁንም ሜዳዎቿ ፍቃድ ስላላገኙ ከሩዋንዳ ጋር ነሐሴ 20 የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም እንደምታደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።