ዋልያዎቹ ለቻን የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል

በቻን ማጣርያ የመጨረሻው ዙር ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ ጀምሯል።

በአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮን ሺፕ ውድድር የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን የደቡብ ሱዳን አቻውን በድምር ውጤት 5ለ0 ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስቀድሞ በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን ነሐሴ ወር መጠናቀቂያ ላይ ከሩዋንዳ ጋር እንደሚያደርግ ይታወቃል።

ለዚህ ጨዋታ እንዲረዳቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከቀናት በፊት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበው በትናትናው ዕለት እና ዛሬ ማረፎያቸውን በጁፒተር ሆቴል በማድረግ በጂም ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተው የሜዳ ተግባራት ዝግጅታቸውን ወደ ሚያደርጉባት አዳማ ከተማ ከሰዓት ገብተዋል። ከደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ ከነበረው ስብስብስ ምንም አይነት ለውጥ ያልተደረገ ቢሆንም በትናትናው ዕለት ሱራፌል ዳኛቸው ባጋጠመው ጉዳት ከስብስቡ ውጭ መሆኑን ተከትሎ በምትኩ ወንድማገኝ ኃይሉን በመተካት ከ10:30 ጀምሮ በአደማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዳቸውን ጀምረዋል።


ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በፈጀው የዛሬው ልምምድ ምኞት ደበበ በግል ጉዳይ ምክንያት ፍቃድ በማግኘቱ ያልተገኘ ሲሆን የተቀሩት ሀያ ሁለቱ የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን ሰርተዋል። ኳስን መሰረት አድርጎ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ልምምድ የከወነው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይም ቀናት እስከ ነሐሴ 18 ድረስ በዚህ መልኩ ዝግጅቱን እያደረገ የሚቀጥል ይሆናል።


ኢትዮጵያ ሁለቱንም ጨዋታዎች ከሜዳዋ ውጭ ስታደርግ የመጀመርያ ጨዋታዋን ነሐሴ 20 በታንዛንያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ላይ አከናውና የመልሱን ጨዋታ ነሐሴ 29 ሩዋንዳ ላይ እንደምታደርግ መገለፁ ይታወሳል።