ዋልያዎቹ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

ከሩዋንዳ አቻው ጋር የቻን ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ቡድኑ ደቡብ ሱዳንን 5ለ0 አሸንፎ ከፊቱ ያለበትን የሩዋንዳ ጨዋታ እየተጠባበቀ የሚገኝ ሲሆን ከጨዋታው በፊትም ከዩጋንዳ አቻው ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ሊያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት የመጀመርያው ጨዋታ ሐሙስ ነሐሴ 12 የሚደረግ ሲሆን ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 14 ይከናወናል። ሁለቱም ግጥሚያዎች አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ላይ የሚደረጉም ይሆናል።

በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በቻን ውድድር የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ ከታንዛንያ አቻው ጋር ይጠብቀዋል።