የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በቀረቡለት አቤቱታዎች ዙርያ ውሳኔ አስተላለፈ

በመጪው ነሐሴ 22 በጎንደር ከተማ ለሚከናወነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በግንቦት ሰባቱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተሰየመው የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በምርጫው ዙርያ የቀረቡለትን አቤቱታዎች መርምሮ ውሳኔ አስተላልፏል።

የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የቀረቡለትን የ4 አቤቱታ አቅራቢዎች መረጃዎችን ሰኞ ነሐሴ 02/2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተረክቦ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመመርመር ችሏል፡፡ ኮሚቴው ይግባኝ ያቀረቡት አካል ተገቢነት ፣ የይግባኙ ጭብጥ ፣ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔ ፣ የኢ.እ.ፌ መተዳደሪያ ደንብ የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብንና ሌሎችን ተያያዥ መመሪያዎችን በመመልከት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ውሳኔ 1

ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ጽ/ቤት በወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ዙሪያ እና ሌሎች እጩዎቻቸውን በተመለከተ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ጽ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም መሰረት በተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን የፕሬዚዳንት እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የምርጫ ማስፈፀሚያ ደንብ አንቀፅ 11 መሠረት የኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑን በሚደነግገው መሠረት ክልሉ ለሥራ አስፈፃሚነት ከላኳቸው ሁለት እጩዎች በተጨማሪ አንድ እጩ ለሥራ አስፈፃሚነት እንዲያቀርብ እና መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አሟልተው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ “33” ንዑስ አንቀጽ “5” መሠረት እጩዎቻቸውን በሁለት ቀናት ውስጥ ማለትም ነሐሴ 9 እና 10 ቀን 2014 ዓ.ም አሟልተው እንዲያቀርቡና የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህንኑ እንዲያስፈፅም ተወስኗል፡፡

ውሳኔ 2

የጋምቤላ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረቧቸውን ሁለት አቤቱታዎች ማለትም ኢ/ር ኡሎሮ ኡፒያው ኡጁሉ ፣ ኛጆክ ጆንክ ካንግ ፣ ኡጁሉ አደይ የሥራ አስፈጻሚ እጩ ሆነው እንዲቀርቡላቸው እንዲሁም በኢ/ር ኦሌሮ ኦፒየው ኡጁሉ ምትክ አቶ ሳይመን ሙን ወል በእጩነት እንዲተኩ የተጠየቀው ይግባኝ በመመልከት እና ውሳኔ በማስተላለፍ ይህንንም ውሳኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ ለሚመለከተው እንዲያሳውቅ ታዟል።

– በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 40 “ሐ” ተ.ቁ. 1 “ሀ” መሠረት በአምስት አባላት ተደግፎ ያልቀረበ እጩ ተቀባይነት እንደሌለው በሚደነግገው ደንብ መሠረት ይህንን ሟሟላት ስላለባቸው በስራ አስፈፃሚ እጩነት የቀረቡት ኢ/ር ኦሌሮ ኦፒያው ኡጁሉ፣ አቶ ኛጆክ ጆንክ ካንግ፣ አቶ ኡጁሉ አደይ በሁለት ቀናት የጊዜ ገደብ ማለትም ነሀሴ 9 እና 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት አሟልተው እንዲያቀርቡና የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህንኑ እንዲያስፈፅም ተወስኗል።

– በኢ/ር ኦሌሮ ኦፒየው ኡጁሉ ምትክ አቶ ሳይመን ሙን ወል በእጩነት እንዲተኩ የተጠየቀው ይግባኝ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የፕሬዝዳንትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማስፈፀሚያ ደንብ አንቀዕ “11” የእጩዎች የይግባኝ አቀራረብ ሥርዓት ተራ ቁጥር 1 መሠረት “በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀርቦ የታዩ አቤቱታዎች ለምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ብቻ ይቀርባል” በሚለው ድንጋጌ መሠረት ይህ አቤቱታ በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀርቦ ያልታየ በመሆኑ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ሊያየው እንደማይችል ተወስኗል።

ውሳኔ 3

በአቶ ገዛኸኝ ወልዴ ካሳሁን የቀረበው የእጩ ፕሬዘዳንት ተወዳዳሪነታቸው እንዲረጋገጥ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የተጠየቀው ይግባኝን በመመልከት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም በተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴፌሸን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማስፈፀሚያ ደንብ አንቀጽ 11 የእጩዎች የይግባኝ አቀራረብ ስነ ስርዓት በተራ ቁጥር “1” “በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀርበው የታዩ አቤቱታዎች ለምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ብቻ ይቀርባል” በሚለው ድንጋጌ መሠረት የአቶ ገዛኸኝ ወልዴ ካሳሁን እጩነት የምርጫው አስፈጻሚ ኮሚቴው ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም የፕሬዘዳንት የሥራ አስፈጻሚ አጩዎችን ባሳወቁበት የስም ዝርዝር ውሰጥ ስማቸው ያልተካተተ በመሆኑ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ በይግባኝ ባዩ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ካሳሁን እጩነት በተመለከተ ያቀረበው አንዳችም ነገር ባለመኖሩ ይግባኛቸውን ለመመልከት የማይችል መሆኑን ወስኗል።

ውሳኔ 4

አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ እና የአፋር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት አቶ አሊሚራህ መሐመድን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ለኢትዮጵያ አግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት የኢ.እ.ፌ የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ተመልከቶ ውሳኔ ሰጥቷል።

አቶ አሊሚራህ ያቀረቡት ይግባኝ አቤቱታ በፌዴሬሸኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 40 ፊደል “ሀ” ተራ ቁጥር “3” መሠረት “ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በማንኛውም ጊዜ በተለያዩ ወይም በተከታታይ ከሦስት የምርጫ ዘመን በላይ ድጋሚ መመረጥ አይችልም” በሚለው መሠረት አመልካቹ ሕጉ እኔን አይመለከተኝም የሚሉት ሕጉ “በማንኛውም ጊዜ” ከሦስት የምርጫ ዘመን በላይ ያገለገለ እጩ ሆኖ መቅረብ አይችልም ስለሚል ይግባኝ ባዩ ያቀረቡት የመጀመሪያ ጭብጥ ተገቢ አለመሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡ ሌላው የሕግ ስህተት ተፈጸመብኝ ያሉትን ጭብጥ በተመለከተ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው የወሰነው ውሳኔ ከፌዴሬሸኑ መተዳደሪያ ደንብና የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብ አንጻር የተፈጸመ የሕግ ስህተት አለመኖሩን ለመረዳት ችናል፡፡ በዚህም መሰረት በተሻሻለው የፕሬዘዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የምርጫ ማስፈጸሚያ ዴንብ አንቀጽ “11″ መሠረት የእጩዎች የይግባኝ አቀራረብ ስርዓት መሠረት የኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑን በሚደነግገው መሠረት አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ያቀረቡት ይግባኝ በዚህ ውሳኔ በተራ ቁጥር “5” ትንታኔ መሠረት ይግባኛቸውን ውድቅ እያደረግን ፤ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰጠው ውሳኔ ትክhል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

ምንጭ : የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን