የዋልያዎቹ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የቀን ለውጥ ተደርጎበታል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር የሚያደርገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ የቀን ለውጥ መደረጉ ታውቋል።

በአልጄርያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የቻን ውድድር የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ነሐሴ 20 እና 29 ለሚኖረው ወሳኝ ጨዋታ ልምምዱን በአዳማ ከጀመረ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

ለዝግጅቱም ይረዳው ዘንድ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሐሙስ ነሐሴ 12 እና ቅዳሜ 14 ቀን እንደሚያደርግ አስቀድሞ መርሐ ግብረ መውጣቱ ይታወሳል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘቸው መረጃ ከሆነ የሐሙስ ነሐሴ 12 ጨዋታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ጨዋታ በአንድ ቀን ተሸጋሽጎ ወደ እሁድ ነሐሴ 15 መቀየሩን አውቃለች። 

ሁለቱም የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ አስር ሰዓት ላይ የሚደረጉ ይሆናሉ።