በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና ወደ ፍፃሜ ያለፉ ክለቦች እና ክልሎች ተለይተዋል

በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ውድድር ላይ ወደ ፍፃሜ ያለፉ ክለቦች እና ክልሎች ተለይተው ታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ከነሀሴ 1 ጀምሮ እየተደረገ የሰነበተው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ወደ ፍፃሜው የተሸጋገሩ ክለቦች እና ክልሎችን ለይቶ አሳውቋል፡፡

በክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋንጫ ይጫወታሉ፡፡

ረፋድ 3 ሰዓት ሲል ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከዕረፍት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት ሲሆን ቀዳሚ የሆኑበትንም ጎል አግኝተዋል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ብሩክ ኤልያስ ወደ ጎል አክርሮ መትቶ በግብ ጠባቂ ሲመለስ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ሀሮን አርተር በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጧት የፈረሰኞቹ ታዳጊዎችን መሪ አድርጓል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሀዋሳዎች በተሻለ የማጥቃት ሀይል ቢጫወቱም ኳስ ከመረብ ጋር ማገናኘት ተስኗቸው ታይቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ሀዋሳ ከተማ ብልጫን ወስዶ መንቀሳቀስ ቢችልም በመከላከሉ ረገድ ደካማ ሆነው በመታየታቸው በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ሰለሞን ታደሰ ተጨማሪ ጎል አክሎ ፍልሚያው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡

ሌላኛው የፍፃሜ ተፈላሚን የሚለየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ እልህ አስጨራሽ የሜዳ ላይ ፉክክርን አሳይቶን በመጨረሻም በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ በሚመራው ንግድ የበላይነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ከዕረፍት መልስ ሦስት ጎሎችን መመልከት ያስቻለን ይህ ጨዋታ ገና አጋማሹ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ (46ኛው ሰከንድ) ላይ የንግድ ባንኩ የመስመር አጥቂ አቤንኤዘር በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታው ተከላካዩ ታምራት አንጄሎ ለማውጣት ሲሞክር በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ንግድ ባንክን መሪ አድርጓል፡፡

ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በተከታታይ ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ብሩክ ስዩም መረጋጋት ተስኗቸው የታዩት ድቻዎች ላይ ሁለተኛ ጎልን አክሏል፡፡ ወላይታ ድቻዎች 60ኛ ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ቢኒያም ዳልጋ በማምከኑ ቡድኑ ወደ ጨዋታ የመመለስ ዕድሉን አምክኖታል። የሆነው ሆኖ ጨዋታው ተገባዶ በጭማሪ ደቂቃ አቤንኤዘር መንግስቱ እጅግ አስገራሚ ጎል አክሎ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ የፊታችን ቅዳሜ ረፋድ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዋንጫ ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ ለደረጃ በክለቦች መካከል የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

በምድብ መርሐ-ግብር የተገናኙት ሁለቱ የክልል ቡድኖች ዳግም በፍፃሜው ይፋጠጣሉ፡፡

ተመጣጣኝ እድሜ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ይዘው ከቀረቡ ክልሎች መካከል የሚጠቀሱትን አዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልልን ያገናኘው ጨዋታ ከተያዘለት ደቂቃ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆን ዘጠና ደቂቃ ሙሉ እጅግ ለተመልካች ሳቢነቱ ያልቀነሰ እንቅስቃሴን አሳይቶናል። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ሲሆኑ ለዚህም ማሳያ የሆኑበት ጎል 11ኛው ደቂቃ ላይ በአጥቂ ሰይፈዲን ረሺድ አማካኝነት አግኝተዋል፡፡ 26ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ሀምዛ ሱልጣን ተጨማሪ ጎል አክሎ የመዲናይቱን ቡድን ወደ 2ለ0 ቢያሸጋግርም 40ኛው ደቂቃ እዩኤል ታሪኩ ኦሮሚያን ወደ ጨዋታ የምትመለስ ጎል አክሎ ጨዋታው ወደ 2ለ1 ተሸጋግሯል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አዲስ አበባ ከተማዎች በመከላከሉ ደካማ ሆነው መታየታቸው መነቃቃትን ይዘው ወደ ሜዳ ለተመለሱት ኦሮሚያ ክልሎች እጅጉን አመቺ ሆኖላቸው ተስተውሏል፡፡

63ኛው ደቂቃ ላይ ሰይፈዲን ረሺድ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል ከመረብ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ ሀምዛ ሱልጣን 71ኛው ደቂቃ ላይ ለቡድኑ አራተኛ ለራሱ ሁለተኛዋን ጎል ከመረብ አዋህዷል፡፡ የአዲስ አበባን የመከላከል ድክመት የተረዱ የሚመስሉት ኦሮሚያ ክልሎች በ29 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ጎሎችን አስቆጥረው ወደ አቻ ውጤት በአስገራሚ መልኩ ተሸጋግረዋል፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ጁንጂ ሀጂ ሁለተኛ ጎል ሲያስቆጥር 80ኛው ደቂቃ ለገሰ ገመቹ ሦስተኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ የመስመር ዳኛ በአዲስ አበባ ተከላካይ ላይ ጥፋት አስቀድሞ መሰራቱን ችላ ባሉበት ቅፅበት ጁንጂ ሀጂ ለራሱ ሁለተኛ ቡድኑ 4ለ4 ማድረግ የቻለች የአቻነት ጎልን ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው ተገባዷል፡፡

ጨዋታው 4ለ4 መጠናቀቁን ተከትሎ በተሰጠው የመለያ ምት ኦሮሚያ 4ለ2 አሸናፊ መሆን በመቻሉ ወደ ፍፃሜ መርሐ-ግብር አልፏል፡፡

9 ሰዓት ሲል በበርካታ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ጨዋታውን እያደረገ ግማሽ ፍፃሜ ላይ የደረሰው የደቡቡ ቀይ ዛላ ከአማራ ክልል የተገናኘበት ጨዋታ ተካሂዷል፡፡ በመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረው የነበሩት ቀይ ዛላዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ በአድነው አበራ ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ በአስደማሚ ደጋፊዎቹ ታግዞ ወደ ፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ በአጋማሹ ተሽሎ መታየት የቻለው ቀይ ዛላ 40ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱራህማን ሱልጣን አማካኝነት ሁለተኛ ጎልን አግኝቷል፡፡ ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ቀጥሎ አማራ ክልል ከመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸው ድክመት በሚገባ በማሻሻል ሁለት ጎሎችን በፍጥነት አካክሰዋል፡፡ በዚህም በ47ኛው ደቂቃ እሱባለው አወቀ በ52ኛ ደቂቃ ደግሞ የአብስራ ነጋሽ ባስቆጠሩት ጎል 2ለ2 መሆን ችለዋል፡፡ ጨዋታው ጥሩ ፉክክርን እያስመለከተን ዘልቆ 84ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቀይ ዛላዎች ተቀይሮ በገባው ኤፍሬም ምትኩ ጎል 3ለ2 አሸንፈው የፍፃሜ ተፈላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በፍፃሜው ጨዋታ ቀይ ዛላ በምድብ ተገናኝተው 3ለ2 ከረታው ኦሮሚያ ክልል ጋር መገናኘታቸውን ዕውን ሲሆን አዲስ አበባ እና አማራ ለደረጃ ጨዋታቸውን የፊታችን ቅዳሜ ይከውናሉ፡፡