በድጋሜ ፌዴሬሽኑን የሚመሩት ፕሬዝዳንት ንግግር

👉”ደጋፊዎቼን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው”

👉”ጉባኤው ትንሽ ለሰራነው ነገር በዚህ ደረጃ እውቅና መስጠቱ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል”

👉”የጉባኤው አባላት ራሳቸውን ነፃ ያወጡበት ነገር ነው…የእኔ መመረጥ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ነፃነት ያወጁበት ነው”


👉”ጉባኤያችን ኢ ሲ ኤ አዳራሽ ተጀምሮ ኢ ሲ ኤ አዳራሽ አልቋል”

ስለ ተሰማቸው ስሜት እና ስለ ተዘጋጀው ሰነድ…?

“እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ትልቅም የቤት ስራ እንዳለብኝ ነው የማስበው ና ጉባኤው ትንሽ ለሰራነው ነገር በዚህ ደረጃ እውቅና መስጠቱ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የሚቀጥለው አራት ዓመት ላይ ያቀድናቸውን ነገሮች ሌጋሲ ዶክመቱ ላይ ያስቀመጥናቸው በተለይ የተቋም ግንባታ ፣ የብሔራዊ ቡድኑ የልምምድ ካምፕ ፣ ከምንም በላይ ደግሞ እንደ ግል ልጆቼ የማያቸው የፓይለት ፕሮጀክቱ ልጆች እሱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ እፈልጋለሁ፡፡ የሴቶች ልማት ላይ የተጀመሩ ስራዎች አሉ፡፡ አዲስ ስራዎች አይደሉም። ግን ደግሞ የጀመርናቸውን ነገሮች የዚህ አመራር አካል ሆኜ ለማስቀጠል አዲስ ስለማይሆንብኝ ትለቅ የቤት ስራ ነው የተሰጠኝ። እጅግ አድርጌ ነው የማመሰግነው ክብሩን እግዚአብሔር ይውሰድ ማለት እፈልጋለሁ”፡፡

ከሁለቱ ተቀናቃኞች የምትወስዱት ሀሳቦች ይኖራሉ…?

“አይደለም ያገባኛል ብሎ ለአመራርነት ከተወዳደሩት ሰዎች ሀሳብ መውሰድ ይቅርና ለሌላም ግብአቶችን እኔ በዚህ እታወቃለሁ ክብር አለኝ፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮችን ለመውሰድ ወደ ኋላ አንልም። ለሀገር ይጠቅማል እስካልን ድረስ ይሄንን አለመውሰድ ንፉግነት ነው የሚሆነው። ክብር አለኝ። አይተሀል ተንከባክቤ ነው ወደ አዳራሹ ያስገባዋቸው። ይሄ ምንም አያጠያይቅም ነገር ግን ስራው ትልቅ የቤት ስራ ያለው እና አሁን ውጫዊ አካሉ ትላንት እና ከስብሰባው በኋላ ከተማው ውስጥ ያደርጉት የነበሩት ነገሮች በወሬ ሳይሆን ትላንት ደግሞ አፈንግጦ በግልፅ የወጣበትን ሁኔታ ሳይ በእውነት በዚህ ደረጃ ይሄን የሚያክል ድምፅ አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ ይሄ የሚያስረዳኝ ጉባኤው ራሱ የጉባኤው አባላት ራሳቸውን ነፃ ያወጡበት ነገር ነው ብዬ የማስበው። የእኔ መመረጥ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ነፃነት ያወጁበት ነው፡፡ ወደፊት እንደዚህ አይነት ድርጊቶች መቅረት አለባቸው፡፡ እንደዚህ አይነት መጠላለፎች መቅረት አለባቸው። ያጠፋ ሰው ይታረማል ፤ መልካም ካላደረገ ደግሞ በስራው ነው መወዳደር ያለበት እንጂ እንደዚህ በጎንዮሽ የሚኬዱ ነገሮች መልካም ስላልሆኑ ሀገራችንን አይጠቅምም። ለየትኛውም ኢንደስትሪ አይጠቅምም ፤ እግዚአብሔር ልቦና ይስጣቸው ማለት እፈልጋለሁ።”

ብሔራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ የሚጫወትበትን ዕድል ስለመፍጠር …?

“እኔ ለመመረጥ ስወዳደር ለምርጫ ግብዐት ብዬ ሜዳ ሰራለሁ የሚል ቃልም አልወጣኝም፡፡ ምክንያቱም ትላንት ሲገለፅ እንደነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የተቋቋመበት ዐላማ አለው፡፡ ከእርሱ ዐላማ በመነሳት እንደውም መራጩን ማታለል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከአሁን በኋላ በድፍረት ልናገር የምችለው ከመንግሥት ጋር በልዩ መልኩ ዋና ስራዬ አድርጌ በመቀራረብ እነኚህ ስታዲየሞች የሚያልቁበት በተለይ የባህርዳር ስታዲየም ከክልሉ መንግሥት ጋር በጣም በመቀራረብ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ወደ አንድ ደረጃ ብሔራዊ ቡድኑ ወደዚህ የሚመለስበትን መንገድ መፈለግ ካልተቻለ ጫናው በግንባር ቀደምነት እኔ እና ፌድሬሽኑ አመራሩ ላይ ነው የሚመጣው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ወጪ ብሔራዊ ፌድሬሽኑ ነው ሽፍኖ ወደ ውጪ የሚልከውና ዋና ስራችን ነው የሚሆነው። ተሰዶ ውጪ የሚጫወት ብሔራዊ ቡድን የሚመለስበት ቀን እኔም ናፍቆኛል። ብሔራዊ ቡድንን ወደዚህ የመመለስ ድርሻ የእኔ ብቻ አይደለም። የሁላችንም ነው። የገንዘብ እጥረት እንኳን ካለ ቴሌቶን ማሰባሰብ ነው። ይሄ ሁላችንንም የሚናፍቅ ጉዳይ ነውና እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተን ነው የምንሰራው። ራሴን እቆጥብ የነበረው ለምርጫ ፍጆታ ተብለው የሚወሩ ነገሮችን አልፈልግም ፤ ውሸት አልወድም። ዋሽተህ እንኳስ ስታዲየም መገንባት አደለም ሜዳ ማስጠረግ ካልቻልክ ትዝብት ላይ ነው የምትወድቀው። ሚዲያውም እያወቀ ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አያምጣ ፤ ወደ መንግስት አካል ውሰዱት። ሚዲያ የእኛ አንደበት፣ ዐይን እና ጆሮ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ቡድናችን እንዲመለስ የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል። እዚህ ላይም ትኩረት አድርጌ ከመንግስት ጋር እሰራለው። ይሄ ከማንም ኢትዮጵያዊ በላይ ይሄ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው ፤ ምክንያቱም ጫናው ቀጥታ እኔ የምመራውን ተቋም ላይ ስለሚመጣ።”

ከውጤቱ ጋር ተያይዞ…?

“ደጋፊዎቼን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው ፤ ላልመረጡኝ የጉባኤው አባላትም እኔ ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስለሆንኩ የእነሱም ፕሬዝዳንት ነኝ። ስለዚህ ከእነርሱም ጋር ተቀራርቤ እሰራለው። ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ኢሳይያስ ቂመኛ አይደለም። ስለዚህ ተቀራርበን በሆደ ሰፊነት አብረን አቅደን እንሰራለን።”

የመጀመሪያ ሥራቸው ምን እንደሚሆን…?

“የብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ ከአሠልጣኙ ጋር ተያይዞ ስራ ከጀመርን ቆይተናል። ከሚመጣው አመራር ጋር ሆነን የእሳቸውን ውል እናስቀጥላለን። ምክንያቱም ለአፍሪካ ዋንጫ ከ8 ዓመታት በኋላ ያሳለፈንን፣ ግብፅን ያሸነፈ እንዲሁም ለቻን ለማለፍ 90 ደቂቃ የቀረውን አሠልጣኝ ማባረር ውጤቱን አለመፈለግ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይሄ ይሆናል። ቀጣይ በ6 ወር ውስጥ የሚሰራው ስራ የጽሕፈት ቤቱን ማስተካከል ነው።”

ዛሬ ስለነበረው የምርጫ ሂደት…?

“ክብሩ በጣም ይለያያል። የዛሬ 4 ዓመት እና ዛሬ ያለው ነገር በጣም ይለያያል። ዛሬ የጉባኤው አባላት በአግባቡ የሚሰሩትን ያወቁበት ነው። የዛሬ 4 ዓመት እና ዛሬ ጉባኤው የነበረው ድምፀት እና ስርዓት ራሱ ይለያያል። ይሄ ማለት ጉባኤው እያደገ መምጣቱን ነው የሚያሳየው። ታዛቢ እንደ ጉባኤ አባል እንደፈለገ ሀሳብ የሚሰጥበት ነበር። ይሄንን ስርዓት እያሲያዝን መጥተን ጉባኤያችን ኢ ሲ ኤ አዳራሽ ተጀምሮ ኢ ሲ ኤ አዳራሽ አልቋል። እያደገ እና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን እያጠበቀ መምጣቱን ነው የሚያሳየው።”

ተቋሙ ላይ ስለሚሰሩት ነገር…?

“ቢሮውን አፍርሶ መስራት ሳይሆን የጽሕፈት ቤቱን እንደ አዲስ ማደራጀት ነው። እዛ ጋር ሪፎርም ካልተሰራ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ይሄ ነው የመጀመሪያ እርምጃዬ የሚሆነው።”