ሀዋሳ ከተማ የሩጫ መርሐ-ግብር አካሄደ

“ክለባችን ኩራታችን” በሚል መሪ ቃል የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ማህበር ያዘጋጀው የሩጫ መርሃግብር በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ ተከናውኗል፡፡

 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከጅምሩ ከ1990 አንስቶ እየተካፈለ የሚገኘው እና የሊጉን ክብር በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ዋንጫን እንዲሁ በማሸነፍ ከክልል ክለቦች ቀዳሚየሆነው የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ክለቡን ለመደገፍ በዛሬው ዕለት “ክለባችን ኩራታችን” በሚል መሪ ቃል ያሰናዱት የጎዳና ላይ ሩጫ መርሃግብር ረፋድ ላይ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል፡፡


በመርሀግብሩ ላይ የክለቡ የበላይ ጠባቂ እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ፣ ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሚልኪያስ ብትሬን ጨምሮ ሌሎች በርከት ያሉ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ የክለቡ ተጫዋቾች ፣ አርቲስቶች ፣ አትሌቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደጋፊዎች ጥምረት ተወካዮች በተጋባዥነት በታደሙበት መርሃግብር ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑ የክለቡ ደጋፊዎች እና የከተማው ማህበረሰብን ያሳተፈው የጎዳና ላይ ሩጫ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ተከናውኗል፡፡


በክለቡ የደጋፊዎች ማህበር በተሰናዳው እና 5 ኪሎ ሜትርን በሸፈነው የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫም በህፃናት እና በአዋቂዎች ተከፍሎ የተከናወነ ሲሆን በውድድሩም ቀዳሚውን ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁትም እንዲሁ ሽልማት ተበርክቷል።


ከዛሬው የሩጫ መርሀግብር ቀደም ብሎ በትላንትናው ዕለት በተመሳሳይ በክለቡ ደጋፊዎች ማህበር አዘጋጅነት ለክለቡ ከ1970 እስከ 2000 ዓመተ ምህረት ድረስ በአሰልጣኝነት ፣ በተጫዋችነት እና በቡድን መሪነት ላገለገሉ ግለሰቦች የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓትን ያከናወነ ሲሆን የዚሁ አካል በነበረ መርሃግብር የቀድሞው የክለቡ ተጫዋቾችም ዕርስ በዕርስ በመጫወት ብዙዎችን በትዝታ ወደ ኃላ የመለሱበትን ደማቅ ጨዋታ ማድረግ ችለዋል።