ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል

በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በካፍ የልህቀት ማዕከት ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል።

የ2023 የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ ካፍ በዚህ ውድድር ላይ ሀገራት ተካፋይ እንዲሆኑ የቅድመ ማጣሪያ ድልድል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ሀገራችን ኢትዮጵያ መስከረም ወር ላይ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር የመጀመርያውን የማጣሪያ ጨዋታዋን ለማከናወን መርሐ ግብር ተይዞላታል።

አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙን እና ረዳቶቻቸውን የሾመው ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ ለ35 ተጫዋቾች የመጀመርያ ጥሪ በማድረግ ካሳለፍነው ሰኞ አንስቶ ጠንከር ያለ ዝግጅታቸውን አያት በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከት በመስራት ላይ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮጵያ በዛሬው የልምምድ መርሐ ግብር እንደተመለከተችው ከሆነ ጥሪ ከተደረገላቸው 35 ተጫዋቾች መካከል 17 ተጫዋቾች ብቻ የቡድኑ አካል ሆነው ሲሳተፉ አይታለች። ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከፋሲል ከነማ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ቡድኑን ያልተቀላቀሉ ሲሆን በተጨማሪም በቻን የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታ ሩዋንዳን በገጠመው ስብስብ የተሳተፉ ተጫዋቾች የቡድኑ አካል መሆን አልቻሉም።

ከረፋድ አራት ሰዓት ጀምሮ ለሁለት ሰዓት በቆየው የዛሬው ልምምድ ጠንከር ያለ አካል ብቃትን መሠረት ያደረገ ተግባራትን ሲፈፀረሙ ተመልክተናል። አስቀድሞ ጥሪ ከተደረገላቸው 35 ተጫዋቾች መካከል ጥሪ ያልተደረገላቸው አማካይ ቡጣቃ ሻመናን ከአርባምንጭ ከተማ ከ20 ዓመት በታች ቡድን እንዲሁም አጥቂ አብዲሳ ጀማል ከአዳማ ከተማ ጥሪ ተደርጎላቸው ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰሩ ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በልምምድ ሰዓት በመገኘት ተጫዋቾቹን ከማነቃቃት ባሻገር ቡድኑ ያለበትን ሁኔታ ለመታዘብ ችለዋል። በካፍ የልህቀት ማዕከል ለሳምንታት በሚቀጥለው የብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ከግማሽ በላይ ጥሪ ተደርጎላቸው ቡድኑን እስካሁን ያልተቀላቀሉ ተጫዋቾች መኖራቸው ለአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ትልቅ ተግዳሮት እንደሚሆን ይገመታል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን መስከረም ወር እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።