የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው መግለጫ ሰጥቷል

👉 “ምርጫው በዚህ መልኩ መጠናቀቁ ትልቅ ድል እና እፎይታ ነው የፈጠረው ፤ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እና ምንም አይነት እንከን የሌለው ነበር ” አቶ በለጠ

👉 “የምርጫ ቦታ መቀየሩን ስናውቅ የወቅቱን ፕሬዝዳንት እና የጽሕፈት ቤት ሀላፊውን አስጠርተን ምክንያታቸውን እንዲያስረዱን አድርገናል” አቶ ኃይሉ

👉 “ይህን አስፈፃሚነት ለቀን እንድንወጣ እና ራሳችንን እንድናገል ከውጭ ከፍተኛ ግፊት ተደርጓል ፤ በርካታ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች ቤተሰባችን ድረስ ደርሰውብናል” አቶ በለጠ

👉 “በዛን ዕለት ልክ በመምጣቱ ደስ አሰኘኝ መሰለኝ ምልክት ያሳየሁበትን ምስል ቆረጥረጥ አድርገው በሚገርም ፍጥነት ‘አቶ ኢሳይያስ ሲያሸንፍ የተሰጠ የደስታ ስሜት’ ብለው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያዘዋውሩት ነበር” አቶ ኃይሉ

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያን እግርኳስ በፌዴሬሽኑ በፕሬዝዳንትነት እና በሥራ-አስፈፃሚነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች ምርጫ መከናወኑ ይታወቃል። ይህንን ምርጫ ሲያስፈፅም የነበረው ኮሚቴም በየጊዜው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ከምርጫው በኋላ ደግሞ በዛሬው ዕለት የምርጫውን ሂደት እና አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ እና ምክትል ሰብሳቢው አቶ በለጠ ዘውዴ ተገኝተው ለአንድ ሰዓት ተኩል የተጠጋ ሀሳባቸውን አጋርተዋል። በቅድሚያም ዋና ሰብሳቢው መድረኩን ተረክበው ዘለግ ያለ ማብራሪያ መስጠት ይዘዋል።

“ምርጫውን የማስፈፀም ስራ ግንቦት 7 ቀን ተመርጠን ሰኔ 14 ከጀመርን በኋላ ጉዳዩን በሦስት ምዕራፍ ከፋፍለን ነበር ማከናወን የጀመረው። የመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ ነው። በዚህ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ኮሚቴው ራሱን የማዋቀር ስራ ነው የተሰራው። ዋና ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ፀሐፊ መርጠን ካደራጀን በኋላ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን በመተዳደሪያ ደንቡ እና በምርጫ ህጉ ዙሪያ ውይይት አድርገናል። በተለይ የሚያስቸግሩ ነገሮችን በጋራ በመሆን መግባባት ላይ ለመድረስ ሞክረን ወደ ስራ ገብተን ወደ 2ኛው ምዕራፍ ተሸጋግረናል። በዚህ ምዕራፍ ሰፊ ስራ ሰርተናል። በቅድሚያ የኮሚቴውን የሥነ-ምግባር ደንብ አውጥተን የድርጊት መርሐ-ግብር ቀርፀን ካፀደቅን በኋላ በመተዳደሪያ ደንቡ እና በምርጫ ህጉ መሰረት የተወዳዳሪዎች መስፈርትን ተነጋግረን ፎርማቶችን ለጉባአው አባላት ልከናል። እኛ በላክነው መሰረትም እጩ ተወዳዳሪዎች በመተዳደሪያ ደንቡ እና ህጉ መሰረት እንዲልኩ ተደርጓል። በቅድሚያ ከሐምሌ 5 እስከ 18 ቀን ነበር እንዲላክ ያስቀመጥነው። ነገርግን በመጨረሻው የማጠቃለያ ቀን ላይ ከስድስት ክልሎች ውጪ ሌሎች ክልሎች እጩ አላኩም። በተለይ የሱማሌ እና የድሬዳዋ ክልሎች ቀኑ እንዲራዘም በጠየቁት መሰረት እና ሌሎች ክልሎችም አሟልተው ባለማስገባታቸው በአጠቃላይ ከ11 ክልሎች 5ቱ ባለማስገባታቸው ስድስቱን ማወዳደር ምርጫውን ፍትሀዊ አያደርገውም ብለናል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ እና ከክልሎችም ጥያቄ ስለመጣ ለአንድ ቀን አራዝመናል። ይህንን ተከትሎ ሐምሌ 19 ሁሉም ክልሎች በሚባል ሁኔታ እጩዎቻቸውን አቀርበዋል። ከዛ በመቀጠል ሳጥን የማሸግ ስራ ነው የሰራነው። በመቀጠል የተወዳዳሪዎችን የተገቢነት መመዘኛዎች የማጣራት ስራ ከሰራን በኋላ ለፕሬዝዳንትነት 3 ለሥራ-አስፈፃሚነት ደግሞ 26 እጩዎች እንዲያልፉ አድርገናል። ሁለት ክልሎች እና አንድ የአፋር ክልል ተወካይ ጥያቄ አቅርበዋል። በዚህም የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ሁለቱ ክልሎች (ቤንሻንጉል እና ጋምቤላ) ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመንተራስ ቀን ተጨምሮላቸው እጩዎቻቸውን እንዲያስገቡ ሲቀመጥ ከአፋር ክልል የተወከሉትን አቶ ዓሊሚራ መሐመድ በተመለከተ ግን የእኛን ውሳኔ ነው ያፀናው። በዚህም የሥራ-አስፈፃሚን እጩዎች ቁጥር ከ26 ወደ 32 ከፍ እንዲል ሆኗል።

“3ኛው ምዕራፍ ላይ ምርጫውን ለማከናወን የሚረዱ ቁሶች፣ ሰነዶች እና የተለያዩ ነገሮች እንዲዘጋጁ አድርገናል። በዚህም ድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በሚስጥር 14 አይነት አዘጋጅተናል። ምክንያቱም በምርጫው ዕለት የቱን ወረቀት እንደምንጠቀም እንዳይታወቅ ነው። የድምፅ መስጫ ሳጥኑንም በመስታወት አድርገናል። የምርጫ ቦታው እኛ ጎንደር እንደሆነ ነበር የምናውቀው። ቦታ መቀየሩን ስናውቅ የወቅቱን ፕሬዝዳንት እና የጽሕፈት ቤት ሀላፊውን አስጠርተን ምክንያታቸውን እንዲያስረዱን አድርገናል። በምክንያቱ እኛ ሙሉ ለሙሉ ባንስማማም ቦታውን የመወሰን ስልጣን ስለሌለን ዝግጅታችንን አዲስ አበባ ላይ አድርገን ቀጥለናል። እኛ ላይ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ላይ የተለያዩ አካላት ጥያቄዎች እየተነሱ እሱን እያቻቻልን ስራችንን ስንሰራ ቆይተን ነሀሴ 21 ከሰዓት ኢ ሲ ኤ አዳራሽን ተረክበን እስከ ምሽት ድረስ የመጨረሻ ስራችንን ስንሰራ ቆይተን ወደ ምርጫው አምርተናል።

“ነሐሴ 22 ጠዋት 3 ሰዓት ምርጫ ከማከናወናችን በፊት ‘የፊፋ እና ካፍ ተወካዮች ይፈልጓቸዋል’ ተባልን። ስንገናኝ በ2 ጉዳዮች ላይ ነው ውይይት ያደረግነው። 1ኛው ዝግጅታችን ምን እንደሚመስል እና ተወዳዳሪዎችን የለየንበትን መንገድ ነበር ያስረዳናቸው። ከእኛ ወገን 32 የስራ አስፈፃሚ እና 3 የፕሬዝዳንት እጩዎችን እናዳስቀረን ነግረናቸው። ነገርግን ትናንት 1 አባል በጉባኤው ለተወዳዳሪነት እንዲቀርብ እንደተወሰነ አስረዳናቸው። በዋናነት የአቶ ዓሊሚራን ጉዳይ ጠቅላላ ጉባኤው ማየት እንደማይችል ነግረናቸው ጉባኤው ያወጣውን መተዳደሪያ ደንብ እንኳን እንደማያውቅ አስረዳናቸው። በተለይ አንድ ግለሰብ ለ3 ጊዜ መወዳደር እንደማይችል በመተዳደሪያ ደንቡ ተቀምጦ እያለ ውሳኔው መወሰኑ ተገቢ እንዳልሆነ ተነጋግረናል። ሁለተኛው የምርጫ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የሚወስነው ውሳኔ የመጨረሻ ነው የሚል ህግ አለ። ስለዚህ የጉባኤው ውሳኔ እነዚህን 2 መተዳደሪያ ደንቦች ጥሶ የወሰነው ውሳኔ ልክ አደለም ብለን መልስ ሰጥተናቸው የፊፋ እና ካፍ ሰዎች በእኛ ውሳኔ ደስተኛ ነበሩ። ምርጫው ላይ የአቶ ዓሊ ጉዳይ ትንች ነገር አስነስቶ ነበር። ግን የፊዋው ተወካይ ጉባኤውን አሳስቦ ወደ ምርጫው ተገብቷል።” ካሉ በኋላ ለምክትል ሰብሳቢው ዕድል ከመስጠታቸው በፊት ከምርጫው በኋላ በግላቸው እየተነሳባቸው ስለነበረው ጉዳይ (ደስታ አገላለፅ) ተከታዩን ብለዋል።

“የመራጮች የምርጫ ወረቀቱ ጋር የተገናኘ ነው። በወቅቱ 138 መራጮች ነበሩ። ወረቀቱ 139 ቢሆን ኖሮ ምርጫው ይደገም ነበር። ካነሰ ግን ችግር የለውም። ይህ ህጉ ላይ የተቀመጠ ነገር ነው። በዛን ዕለት ልክ በመምጣቱ ደስ አሰኘኝ መሰለኝ ምልክት ያሳየሁበትን ምስል ቆረጥረጥ አድርገው በሚገርም ፍጥነት ‘አቶ ኢሳይያስ ሲያሸንፍ የተሰጠ የደስታ ስሜት’ ብለው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያዘዋውሩት ነበር። ይሄንን ልጄ ነች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አይታው የነገረችኝ። ይህ የሚገርም ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን እኛ ላይም የተገቢነት ጉዳዮች ሲነሱ ነበር። እርግጥ ምርጫ አደለም አፍሪካ ውስጥ ሌላም ቦታ የሆኑ መጠላለፎች አይጠፉትም። እኛ ጋር ግን ትንሽ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው ያለው። እኛ ግን ስራውን አምነንበት ስለገባን ችግር የለውም። የሚመጣውንም ነገር ለመቋቋም መሸከም ግድ ስለሆነ ምንም አልመሰለንም።” በማለት ተናግረዋል። በምርጫው ሂደት ያጋጠሟቸውን ነገሮች ለቀጣይ እንዳይደገም ዶክመንት እያዘጋጁ እንደሆነ ጠቁመው ዕድሉን ለአቶ በለጠ ሰጥተዋል።

“ከምርጫው በፊት እና በኋላ የተለያዮ አስተያየቶች እንደሚነሱ እናውቃለን። ምርጫው በዚህ መልኩ መጠናቀቁ ትልቅ ድል እና እፎይታ ነው የፈጠረው። ምክንያቱም ብዙ የተባሉ ነገሮች ነበሩ። ነገር ግን ይህ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ እና ምንም አይነት እንከን የሌለው ሆኖ ተካሂዷል። ከምርጫው በፊት ሳንናገራቸው የነበሩ ነገሮች አሁን መናገር የምፈልገው ይህን አስፈፃሚነት ለቀን እንድንወጣ እና ራሳችንን እንድናገል ከውጭ ከፍተኛ ግፊት ተደርጓል። ነገር ግን ጠቅላላ ጉባው የጣለብንን እምነት ጥለን ስለማንወጣ የሚመጣብንን ነገር በፀጋ ተቀብለን ምርጫውን ለማስፈፀም ችለናል። በርካታ ዛቻዎች፣ ማስፈራሪያዎች ቤተሰባችን ድረስ ደርሰውብናል። በሌላ በኩል ህትመትን በተመለከተ ለፌዴሬሽኑ ሳንሰጥ በራሳችን ኮድ ሰጥተን በሚያስፈልግ ሰዓት ስውር ቦታ በመውሰድ የዕረፍት ሰዓት እየሰጠን አምስታችን በመፈራረም በዕለቱ እንዲካሄድ ያደረግነው። ካሜራዎች በሁለት ቦታ እንዲነሱ ያደረግነው መረጃዎች ስለነበሩን ነው። ሰው በነፃነት መምረጥ ስለሚገባው ይህን በማድረጋችን ልንደነቅ ነው የሚገባው። ሰሞኑን እየተደረገ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። ማንም ያሸንፍ ይሸነፍ የኛ ጉዳይ አይደለም። ዋናው ስፖርቱ እንዲቀጥል ነው። አቶ ዓሊሚራህን በተመለከተ ስንወስን ጥላቻ ኖሮን ሳይሆን ፈቅደንላቸው ቢወዳደሩ ኖሮ ምርጫው ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝ ነበር። ዓሊሚራህ ለምን ውድድር ውስጥ እንዲገባ ተፈለገ ምርጫው እንዲሰረዝ ታቅዶ ነው። መወዳደር ካለባቸው ደንቡ ተሻሽሎ በቀጣይ እንዲካሄድ ነው ያደረግነው። በአጠቃላይ መተዳደርያ ደንቡ በተለይ የምርጫ አንቀፅ 33 ፣ 41 በደንብ መታየት መሻሻል ያለባቸው ናቸው።” ብለዋል። በመቀጠል በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተከታዮቹን ጥያቄዎች አንስተው ምላሾች ተሰጥተዋል።

ድምፅን በገንዘብ ለመግዛት ሙከራ የነበረ ስለመሆኑ…

“ድምፅን በተለያየ መንገድ መግዛት እንግዲህ በተለይ ከምርጫው በኋላ ተወዳዳሪዎች ያነሱት ቅሬታ አለ። ከምርጫው በፊት ደግሞ በአንዳንድ አካላት ሚዲያውን ጨምሮ የሚነሱ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ከምርጫው በፊት ይነሳ የነበረው ‘የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን የገንዘብ ማማለያ በማድረግ ድምፃቸውን ለመግዛት ጥረት ይደረጋል’ የሚል ወሬ እንደነበር ማንም ይሰማል እኛም እንደእናንተ እንሰማለን። ግን አንድ ያጋጠመኝን ነገር ልንገራችሁ። ኢሲኤ አዳራሽ ነሐሴ 21 እየተዘጋጀን እያለ ፤ ለ 22 ምርጫ ወደ ምሽት አካባቢ ከፖሊስ ስልክ ተደወለ ፤ ቀጥታ የተደወለው ለእኔ ነው። ማንነቴን ጠየቁኝ ፣ ከየት እንደሚደውሉ ነገሩኝ የፖሊስ ባልደረባ ናቸው። ‘ከድምፅ መግዛት ጋር በተያያዘ አንዳንድ መረጃዎች መጥተው ሰዎችን ይዘን ምርመራ እያካሄድን ነው እና የምርጫ ደንባችሁ ምንድነው የሚለው ?’ ብለው ጠየቁኝ የምርጫ ሕጉን በዝርዝር ነገርኳቸው። ‘ተመራጭ ሆነው ድምፅን በገንዘብ የመግዛት ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ካሉ የምርጫ ኮሚቴው ሥልጣን አለው ፤ እሱን በተመለከተ ፖሊስ የከፈተው የምርመራ መዝገብ እና የደረሰው ተጨባጭ ማስረጃ ካለ ላኩልን። ተመራጮች ካልሆኑ እና መራጮች ከሆኑ ግን እሱንም አጣርታችሁ ንገሩን ፤ ምክንያቱም የመራጮች ጉዳይ አብሮ የሚታይ ስለሆነ’ አልናቸው። ‘አይ መራጭም ተመራጭም አይደሉም’ አሉን። እንደዛ ከሆነ እኔም የደወሉልኝ የፖሊስ ባልደረባም የሕግ ሰዎች ስለሆንን ‘ከዛ ውጪ መደበኛ የወንጀል ሕጉ እንዲህ ዓይነት ተግባሮችን በተመለከተ ያስቀመጣቸው የወንጀል ድንጋጌዎች አሉ እና የምርመራ መዝገባችሁን ከፍታችሁ በዛ መንገድ መሄድ ትችላላችሁ’ በማለት መልስ ሰጥቻቸው ከዛ በኋላ መረጃም የለኝም። ስለዚህ በተለያየ መንገድ የመግዛት ነገር ነበር ወይ ? ወሬ ነው የሚሰማው። በተጨባጭ እከሌ ለእከሌ እንደዚህ አደረገ ተብሎ የደረሰን መረጃም የለም ያወቅነውም ነገር የለም ፤ ፈፅሞ የለም። በአትኩሮት እንከታተል ነበር። ምክንያቱም የምርጫን ድምፅ ለማዛባት የሚደረገው ርብርብ እና ሩጫ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተከታትሎ ይሄን ያደረገውን ወገን እንዲቀጣ ካላደረገ ምርጫውን ሰላማዊ እና ፍትሀዊ አያደርገውም። ምክንያቱም በፍትሀዊነት መመረጥ ይገባል ከተባለና ምርጫው በሰላማዊ መንገድ መሄድ ካለበት እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች መቆም አለባቸው። ለዚህም ነበር በአትኩሮት ስንከታተል የነበረው። ከፖሊሶች ጋርም ስንደዋወል የነበረው ለዚህ ነው ፤ ግን የመጣልን ነገር የለም።”

የምርጫው ቦታ መቀየሩን ስትሰሙ ሙሉ ለሙሉ ስላልተቀበሉበት ምክንያት…

“አንደኛ ድንገት ሆነብን እውነት ለመናገር። ለሥራ አቶ በለጠ ጋር መጥተን ምርጫው እየተደረገ ስለነበርም ‘ቦታው ተቀይሮ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መጥቷል’ ሲባል እኔ እና እሱ ተማከርን ፤ ምርጫውን የምናስፈፅመው ባለቤቶቹ እኛ ነን ስለዚህ መጠይቅ አለብን። አጋጣሚ ሆኖ አቶ ኢሳይያስ እዚህ መግለጫ ሰጥተው ቢሯቸው እንደነበሩ አረጋገጥን። ወዲያው አቶ ባህሩን ‘አቶ ኢሳይያስን ጥራልን’ አልነው እኔ እና አቶ በለጠ ፤ ጠራንና አብራሩልን አልናቸው። ‘ከባድ ውሳኔ ነው የወሰናችሁት ፤ ይህ ውሳኔ የሚያመጣውን መዘዝ ታውቁታላችሁ ወይ ? ምክንያቱም የሚመጡትን ነገሮች ትከሻችሁን ሰፋ አድርጋችሁ ለመቀበል ተዘጋጁ’ አልናቸው። ድንገት ስለሆነብን ግን ደንግጠን ነበር እውነት ለመናገር። ይሄ ነው ያላስማማን እንጂ እነሱ ያስረዱበት መንገድ አስማምቶናል። አንዱ ተነስቶ ‘ጉባዔውን አውከዋለው’ ሲል በአንድ በኃላፊነት ደረጃ ከተቀመጠ ሰው እንዲህ ዓይነት ዛቻ ሲመጣ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተከታትሎ በኢመርጀንሲ ኮሚቴ አማካይነት መወሰኑ እያደርን ስናስበው ተገቢነቱን ነው የተቀበልነው ፤ አዲስ አበባ መሆኑ በተሻለ ግልፅ ሆኖ ምርጫው ማለቁን ተስማምተን ነው ወደዚህ ሥራ የገባነው።”

በሥራ-አስፈፃሚነት የተመረጡት ግለሰብ ‘ራሴን አግልያለው’ ስለማለታቸው…

“ራሳቸውን የማግለል ጉዳይ እሁድ ጠዋት ምርጫውን ስንጀምር ነው የመጣው። ራስን በማግለል ዙሪያ የምርጫ ኮዱ ምንም ነገር አይልም። ለምርጫ እየተዘጋጀን እያለ ‘ራሴን አንስቻለሁ’ ብሎ ሲመጣ ያስደነግጣል። ‘ምን መጣ ?’ ነው የሚያስብለው። ስለዚህ ምንአልባት ትናንትና ሰጥታችሁን ቢሆን ኖሮ ጉዳዩን ኮሚቴው ተሰብስቦ ሊያየው ይችል ነበር። አሁን ኮሚቴው ቁጭ ብሎ የሚወያይበት ጊዜም የለውም። ራስን ከምርጫ ማግለል ከባድ ውሳኔ ነው። በውድድሩ ላይ የሚያመጣው ለውጥም ቀላል አይደለም። ከመተዳደሪያ ደንቡ አንፃርም ከባድ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ቁጭ ብለን ለመነጋገርም ጊዜ አላገኘንም እና ‘ለጊዜው ውሳኔያችሁን አንቀበልም ከምርጫ ኮዱ አንፃር ጥያቄያችሁን ልንቀበል አልቻልንም’ ብለን መልሰናል። የሌላኛውን ወገን ተወዳዳሪ ዕድል ያጠባል ? ያጠባል ! ግልፅ ነው እሳቸው ቢወጡ ሌላ ተወዳዳሪ መጥቶ መወዳደሩ አይቀርም። ግን እኛ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲያልቅ ነው የፈለግነው ፤ ምንም ዓይነት ውጣ ውረድ ሳይመጣ።”

ከደቡብ ኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተያይዞ…

“መተዳደሪያ ደንቡ ‘አንድ አባል አባል ለመሆን ለጠቅላላ ጉባዔው አቤቱታ አቅርቦ ጠቅላላ ጉባዔው አቤቱታውን ከተቀበለው ከዛች ደቂቃ ጀምሮ ሙሉ መብቱን ነው የሚጎናፀፈው። አጋጣሚ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወካይ መጥቶ ሲያናግረን አጋጣሚ ተሰብስበን ሥርዓቱን እየጠበቅን ነበር ፤ ፊፋዎችም የዛን ጊዜ አልመጡም ገና እና ቁጭ ብለን ለመወያየት ጊዜ አገኘን። መተዳደሪያ ደንቡን አውጥተን አየነው የሚከለክል ነገር የለውም። ‘ስንት ናችሁ የመጣችሁት ?’ አልን ‘እኔ ብቻ ነኝ’ አለ። እሱ በምርጫ እንዲሳተፍ አድርገናል። ተገቢ ውሳኔ ነው የወሰንነው።”

የእጩዎች ቀን ስለተራዘመበት መንገድ…

“እስከ 18 ድረስ ስድስት ክልሎች አሟልተው አቅርበዋል። ሶማሌ አንድ ሰው አላሟላም ፣ ጋምቤላ ጭራሽ አላመጣም ፣ ሲዳማ ጭራሽ አላመጣም ፣ ድሬዳዋ አንድ ሰው ብቻ ነው የመጣው ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አንድ ሰው ብቻ ነው የመጣው ፤ ከ11 አምስት ስትቀንስ ስድስት ነው የሚቀረው። አጋጣሚ አቶ በለጠ እና ረሂማ አዲስ አበባ አልነበሩም እና በቨርችዋል ነው ስብሰባውን ያካሄድነው ፤ በቃ ጭንቀት ውስጥ ነው የገባነው። በመጨረሻ 13 የሥራ አስፈፃሚ የምናወዳድረው መተዳደሪያ ደንብ እያለ የትግራይ ክልል አሁን ባለው ሁኔታ ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አባል ባለመሆኑ (ወደ ፊት አባል ይሆናል ተብሎ ነው መተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተካተተው) የስድስት ሥራ አስፈፃሚን አወዳድረን ይህንን ሥልጣን ተረከቡ ማለት በሕግ አያስኬድም ምክንያቱም ውድድሩ በ 11 መካከል ስለሆነ። የሞራል ጉዳይ ግን ይነሳል። ስለዚህ ‘አንድ ቀን መጨመሩ እኛን ምንድነው የሚጎዳን ?’ አልን። ከዚህ በፊት ስንጠየቅም ሁኔታውን እያየን እስከ ከ15 እስከ 18 ድረስ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን እያየን የምንጨምር ከሆነ እንጨንራለን ነው ያልኩት። በዛ መሰረት ነው አንድ ቀን የጨመርነው። አንድ ቀን በመጨመራችን የ11 ክልል ተወዳዳሪዎች ተሟልተው እንዲመጡ ሆኗል። በዚህ በጣም ደስተኛ ነን። ስለዚህ የቱ ነበር የሚጠቅመው ብሎ ሂሳብ መስራት ነው። ስድስት ክልሎችን አወዳድሮ ለ13 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቦታ ማስቀመጥ ነው የሚጠቅመው ወይስ አንድ ቀን ጨምሮ አምስት ክልሎችን ጨምሮ የበቀደም ዕለቱን ዓይነት ምርጫ ማካሄድ ነው የሚቀለው ? ይሄ ነው። ከዛ ውጪ ደግሞ ጥያቄም መጥቶልናል። ቀን ይሰጠን የሚል ፤ ድሬዳዋ ልኮልናል ደብዳቤው አለ። ሴማሌ ልኮልናል። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ከክልሎች እየመጣ ፤ የጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል የፀጥታ ጉዳይን ታውቁታላችሁ ፤ በዚህ ሁኔታ አንድ ቀን መጨመር ፍትሀዊም ነው ፣ ሞራላዊም ነው። ለዚህ ነው አንድ ቀን የጨመርነው። የጨመራችሁት ገዛኸኝን ለማሰናበት ነው ? ሐረሪ ለእኛ አማክሮናል እንዴ ? ገዛኸኝን እንደሚያነሳው ? በምን እናውቃለን እኛ ? ሐረሪ ሰጠው ሐረሪ አነሳው አለቀ። የምናውቀው ነገር የለም። አንድ ቀን የጨመርነው የአምስቱን ክልሎች ለማሟላት ነው። ያ ተሟልቶልናል ሥራችንን ሰርተናል። አንድ የሆነውን ነገር ግን ልንገራችሁ ፤ ይሄን ጉዳይ ደግሜ መናገር ስለማልፈልግ። አቶ ገዛኸኝ ከአዲስ አበባም ድጋፍ አግኝቶ ነበር። የሐረሪ ቀድሞ ገብቶለታል ፤ ቦክሱ ላይ ሲገባ ታስገባለህ ከዛ በኋላ አታስወጣውም። የአዲስ አበባዎች ድንገት ቢገባ ብሎ ለእኛ ‘ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ አዲስ አበባ’ ብሎ ‘አዲስ አበባ ወክሎኛል ፣ ድጋፍ ሰጥቶኛል አመሰግናለሁ። ነገር ግን ድጋፉን ስለማልፈልገው ድጋፉ ቢገባልኝ እንኳን በምርጫ ኮሚቴው ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራው ‘ ብሎ ለእኛ ማመልከቻ አስገብቷል። ይሄን ደብዳቤ ለእኛ ካስገባ እና አዲስ አበባ ድጋፉን ከነሳው በኋላ ሐረሪ ደግሞ አነሳበት ፤ ገዛኸኝ አየር ላይ ቀረ። ይሄን አየር ላይ ያለ ጨዋታ ማን መጫወት እንደነበረበት ግራ ይገባኛል። ከዛ ውጪ ይሄ ጉዳይ ከእኛ ጋር የሚያገናኘውም ጉዳይ የለም። ሐረሪ አይደለም ያነሳበት ? ሐረሪ ሄዶ ለምን አይጠይቅም ? ለምን አነሳህብኝ ብሎ ? አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ነው ጌታዬ ፤ ምንም ሌላ ነገር የለውም። ሐረሪ ለገዛኸኝ ድጋፍ ሲሰጥም አናውቅም ፤ ሲያነሳ ነው ደብዳቤው የደረሰን። ከእኛ ጋር ተማክሮ አይደለም። ስለዚህ የአቶ ገዛኸኝ ከምርጫው መውጣት ምርጫውን ፍትሀዊ አያደርገውም ወይ ? እንዴት አድርጎ እንደማያደርገው እኔ አይገባኝም። እሱን በኋላ ብንነጋገር ይሻላል። ሐረሪ መቼ ነው ያነሳው ከተባለ ፤ በ19 ነው ያነሳው። የተራዘመው ግን ገዛኸኝን ለማሰናበት ሳይሆን ገዛኸኝ እንደሚሰናበትም ስለማናውቅ እነዚህ አምስት ክልሎች እንዲያሟሉ ዕድል ሰጥተን ምርጫው ሙሉ እንዲሆን በማሰብ ነው።

ከምርጫው በኋላ ቅሬታዎች በይፋ ስለመምጣታቸው…

“በሚዲያ ከምንሰማው ውጪ ምንም የመጣ ነገር የለም። እሱም የአቶ መላኩ ነው። አቶ ኢሳይያስ ከምርጫው በኋላ ደስታቸውን ነው ሲገልፁ የሰማሁት። እውነት ለመናገር አልተከታተልኩም።

በመጨረሻም አቶ ሀይሉ ሞላ “የወለዳችሁት ልጅ አድጎ ፤ ትምህርት ቤት ገብቶ ፤ ኮሌጅ ሲጨርስ ደስ እንደሚላችሁ እኛም ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ በመጠናቀቁ ደስ ብሎናል።” በማለት መግለጫቸውን አገባደዋል።