ሀዋሳ ከተማ ለቀድሞው ባለውለተኞቹ የገንዘብ ስጦታን አበርክቷል

የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማኅበር ክለቡ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በአሰልጣኝነት ለመሩት እንዲሁም ክለቡን አገልግለው በህይወት ላለፉ የስፖርተኛ ቤተሰቦች ድጋፍ አድርጓል፡፡

የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማኅበር ባሳለፍነው ሳምንት ክለቡን በፋይናንንስ ለማጠናከር የሩጫ መርሐ-ግብር ያከናወነ ሲሆን በህይወት ያሉትንም ሆነ በህይወት የሌሉትን (ቤተሰቦቻቸውን) በመጋበዝ ነገርግን ክለቡን ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝነት ፣ በቡድን መሪነት እና በተጫዋችነት ላገለገሉ አካላት የዕውቅና ዝግጅት ማከናወኑ ሲታወስ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት ክለቡን ለመሩ እና የክለቡ አካል ለነበሩ የስፖርተኛ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍን ማድረጉ ታውቋል።


የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ሀዋሳ ከተማን በ1996 እንዲሁም 1999 የዋንጫ ባለቤት ላደረጉት እና በአሁኑ ሰዓት የራሳቸውን አካዳሚ በመክፈት እያሰለጠኑ ያሉትን አሰልጣኝ ከማል አህመድ ጨምሮ ክለቡን አገልግለው በህይወት ለሌሉት የቀድሞው የህክምና ባለሙያ መስፍን ላንጋኖ ፣ በ90’ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቡድኑን ላገለገሉት አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው ፣ ክለቡን በተጫዋችነት ማገልገል ለቻለው ሙሴ ዮሴፍ እና ባለንበት የሚሊኒየሙ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ ተጥሎበት በድንገት ህይወቱ ላለፈው ግብ ጠባቂው ክብረአብ ዳዊት ቤተሰቦች ደጋፊ ማኅበሩ የገንዘብ ስጦታን ያበረከተ ሲሆን በቀጣይም በክለቡ አሻራቸውን አስቀምጠው ያለፉትን በጠቅላላ በሂደት እንደሚያመሰግን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡