“በራሳችን እንቅስቃሴ ብልጫ ወስደን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን” አስቻለው ታመነ

ፋሲል ከነማዎች ወሳኙን የቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት አዲሱ የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አምና ቅዱስ ጊዮርጊስን በመልቀቅ ዐፄዎቹን የተቀላቀለው የመሀል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ነገ ክለቡ ፋሲል ከነማ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የብሩንዲውን ቡማሙሩን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሲገጥም ከብሔራዊ ቡድን ቆይታ መልስ አዲሱ የቡድኑ አምበል በመሆን ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ከተጫዋቹ ጋር ቆይታን አድርጋለች፡፡

ስለቡድኑ መንፈስ…

“ያው ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው። ዛሬም እንዳየኸው ነው ፤ የቡድኑ መነሳሳት ጥሩ ነው። እየተዛጋጀን ያለነው ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ ቢሆንም በመሀል ብሔራዊ ቡድን ሄጀ ነበር። ከዛ ስመለስም የነበረው ነገር በጣም ጥሩ ነበር።”

ስለ ተጋጣሚ ቡድን…

“ስለ ተጋጣሚ ቡድን ወቅታዊ መረጃ አለን። በአስልጣኞቹ በኩል እየደረሰን ነው። ጥሩ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። ሊጋቸው እንደጀመረም ሰምተናል። በሊጋቸው ሦስት ጨዋታ አሸንፈው አንድ ጨዋታ አቻ መውጣታቸውን ሰምተናል። በራሳችን እንቅስቃሴ ብልጫ ወስደን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን።”

አምበል ሆኖ ስለመሾሙ…

“በብሔራዊ ቡድንም አምበል ሆኜ መርቻለሁ ፤ በጊዮርጊስ ቤትም እንደዚሁ። አሁን ደግሞ በፋሲል ቤትም ይህን ዕድል አግኝቻለው። ተጫዋቾቹ አብዛኞቹ በብሔራዊ ቡድን የማውቃቸው ናቸው። ያው ክለቡም አምኖብኝ ኃላፊነቱን ሰጥቶኛል። እኔም ኃላፊነቱን በአግባቡ እና በድል በታጀበ መንገድ ነው ማጠናቀቅ የምፈልገው። የተሰጠኝን የአምበልነት ባጅ እጅ ላይ አስሮ መግባት ብቻ ሳይሆን ካለኝ ልምድ በሜዳም ውስጥ ከሜዳ ውጪም ያሉ ነገሮች ለመወጣት አስባለሁ። ከፋሲል ከነማ ጋር በፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ከፍ ማድረግ ፣ በአፍሪካ መድረክም ከዚህ ቀደም ከነበረው ታሪክ የተሻለ ነገር ማድረግ እፈልጋለው።”

ስለወቅታዊ አቋሙ…

“ያው እዚህ ክለብ ስመጣ ብዙ ነገር እንደሚጠበቅብኝ አውቃለሁ። ከጤና ችግር አንፃር መድሃኒት እየወሰድኩ ነው ስጫወት የነበር። ከራሴም ጋር በተያያዘ ትንሽ ኪሎም ጨምሬ ነበር። ያም ያም ስለነበር ብዙም ጥሩ ጊዜ አላሳለፍኩም። አሁን ባለኝ ነገር በሊጉ ወደ መጨረሻ አካባቢ ያሳየሁትን አቋም እንዲሁ ከዚህ በፊት ሚያውቁኝን አስቻለውን ሆኜ በቀጣይ ውድድር ዓመት ይጠብቁኝ።”

ስለነገው ጨዋታ…

“ሁላችንም ውስጥ ያለው የነገውን ጨዋታ በማሸነፍ ለደጋፊዎቻችን የበዓል ስጦታ ማበርከት እንፈልጋለን። ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት በአካል ብቃትም በሥነ ልቦናውም ዝግጁ ነን።”

ለደጋፊዎች መልዕክት…

“የታወቀ ነው ! የፋሲልን ደጋፊ እኔ በነበርኩበት ሰዓት አምና አይቼውለሁ ፤ ሳልኖርም የምሰማው ነገር። ከዚህ በፊት ሽሬ ድረስ ሄዶ ምን እንደተፈጠረ እናውቃለን ፤ እስከ ሞት ድረስ ነው መስዋትነት የሚከፍለው። ዘንድሮም ሀዋሳ ፣ ድሬዳዋ ፣ አዳማ እየመጡ ይደግፉን ነበር። እና እነሱ ለነገው ጨዋታ ይቀራሉ ብዬ አላስብም። ስታዲየሙን ሞልቶ እንደምንጫወት ነው የማስበው። ሁሉም ከያለበት መጥቶ እንዲደግፈን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።”