አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዋልያዎቹ ጋር ይቀጥላሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኮንትራት መራዘሙ ተረጋግጧል።

መስከረም 18 2013 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ተደርገው ተሹመው የነበሩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቡድኑን ይዘው ዘልቀዋል። በቆይታቸው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ያሳኩት አሰልጣኝ አሁን ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ የቻን ውድድር ላይ የሚያሳትፈውን ውጤት እንዲያስመዘግብ አድርገዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ውላቸው የሚያበቃበት ጊዜ መቃረቡ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቃላት ደረጃ እንደተስማሙ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነጋር የቆየ ቢሆንም የኮትራት ማብቂያ ጊዜው መቋረጡ ትኩረትን ስቦ ነበር። ዛሬ ፌዴሬሽኑ ባወጣው መረጃ መሰረት ግን
የአሰልጣኙ ውል ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ብቻ ቢቀረውም ለቀጣዮቹ 24 ወራት ዋልያዎቹን ይዘው እንደሚቀጥሉ ተረጋግጧል።