የባህር ዳር ስታዲየም ወሳኙን የኤል-ሜሪክ እና አርታ ሶላር ጨዋታ ከነገ በስትያ ያስተናግዳል

ከነገ በስትያ በባህር ዳር ስታዲየም የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክ እና የጂቡቲው ክለብ አርታ ሶላር ከተማዋ እየገቡ ሲሆን የስታዲየም መግቢያ ዋጋም ይፋ ሆኗል።

የአህጉራችን የክለቦች ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሀገራት ቡድኖች እንደየደረጃቸው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክም በቅድመ ማጣሪያው ከጂቡቲው አርታ ሶላር ጋር ተመድቧል። ቡድኑም የመጀመሪያውን ጨዋታ ወደ ጂቡቲ አምርቶ 2ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ በሀገሩ ለማድረግ ሜዳ ስላጣ ጨዋታውን በባህር ዳር ስታዲየም ለማከናወን እንደወሰነ ከሳምንታት በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር።

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም ኤል-ሜሪክ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ስታዲየሙን በማከራየት ጨዋታው እንዲከናወን ፍቃድ ሰጥቷል። እንደ ባለሜዳ የሚታየው ሜሪክ ለወሳኙ ጨዋታ ከሦስት ቀናት በፊት ወደ ሀገራችን የመጣ ሲሆን ደብረ ዘይት ላይ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቶ ምሽት 2 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ደረሰ ደርሶ ማረፊያውንም በብሉ ናይል ሆቴል እና ሪዞርት አድርጓል። እንደ አሌክስ ሶንግ እና ሰለሞን ካሉ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በስብስቡ የያዘው አርታ ሶላር በበኩሉ ነገ ረፋድ 4:30 ባህር ዳር እንደሚደርስ ይጠበቃል። ዩጋንዳዊ ዳኞችም ዛሬ 10:30 ከተማዋ ገብተው የጨዋታውን መጀመር እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ተመላልቷል።

ምንም እንኳን ይህ ጨዋታ የሀገራችን ክለቦች ባይሆንም የባህር ዳር እና አካባቢዋ የስፖርት ቤተሰቦች ጨዋታውን እንዲመለከቱ ጥሪ ቀርቧል። ከቪ አይ ፒ መግቢያ ውጪም በሁሉም የስታዲየም ክፍሎች የመግቢያ ዋጋ 30 ብር መሆኑ ተጠቁሟል።