ወልቂጤ ከተማ ከሞደርን ጋዳፊ አማካይ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል

ወልቂጤ ከተማ በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ከተሳተፈው የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ አማካይ ለማስፈረም ተቃርቧል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ የተጠናቀቀው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ ተሳትፎ በማድረግ 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል። በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችም የበርካታ የሀገራችንን ክለቦች ቀልብ ገዝተው ድርድር ሲያረጉ የነበረ ሲሆን ከቀናት በፊትም አጥቂው ቻርለስ ሙሲጊ ድሬዳዋ ከተማን ለመቀላቀል የወረቀት ሥራዎች እየተገባደዱ እንደሚገኝ አስነብበን ነበር። አሁን ድረ-ገፃችን ባገኘችው መረጃ ደግሞ የዚሁ ቡድን ሌላ ተጫዋች ወልቂጤ ከተማን ሊቀላቀል ነው።

ሠራተኞቹን ሊቀላቀል ስምምነት ላይ የደረሰው ተጫዋች ካሶዚ ኒኮላስ ነው። የቀድሞ የካምፓላ ሲቲ ካውንስል (KCCA) የተከላካይ አማካይ ከወልቂጤ ጋር በብዙ ጉዳዮች ስምምነት ላይ እንደደረሰ ሲታወቅ በቅርቡም ከሞደርን ጋዳፊ ጋር ያለውን ውል በስምምነት ቋጭቶ በመምጣት ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።

በተያያዘ የዝውውር ዜና ክለቡ አስራት መገርሳ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ አንዋር ዱላ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ማቲያስ ወልደአረጋይን በይፋ አስፈርሟል።