አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ረዳት አግኝተዋል

ሠራተኞቹ ዋና አሠልጣኛቸው ገብረክርስቶስ ቢራራን እንዲያግዙ ሁለት ረዳቶችን መቅጠራቸው ታውቋል።

በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማ ከነገ በስትያ በሚደረገው የሊጉ ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ስብስቡን በአዲስ መልክ አጠናክሮ የመጀመሪያውን የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር በአሸናፊነት አጠናቆ የሊጉን ጅማሮ እየተጠባበቀ ይገኛል። ክረምት ላይ ቡድኑን የተቀላቀሉት አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም ከክለቡ ጋር በመሆን ዘነበ ፍሰሀ እና ሳዳት ጀማልን በረዳትነት ወደ ስብስቡ ቢያመጡት ዘነበ ፍሰሀ ውስን ልምምዶች ላይ ተሳትፎ ክለቡን ለቆ ሄዷል። ይህንን ተከትሎ አሠልጣኙ ከግብ ጠባቂዎች አሠልጣኙ ሳዳት ጀማል ጋር በመሆን ቡድኑን ሲያሰናዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ረዳት ማግኘታቸው ታውቋል።

በዚህም የአዳማ ከተማን ታዳጊ ቡድን በማሠልጠን የስልጠናውን ዓለም ተቀላቅሎ ለገጣፎ ለገዳዲን እና ዓምና ግማሽ ዓመት ሀምበሪቾ ዱራሜን እንዲሁም ወላይታ ድቻን በረዳትነት የመራው አሠልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ በዛሬው ዕለት ወደ ባህር ዳር በማምራት ቡድኑን በረዳት አሠልጣኝነት እንደተቀላቀለ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ በበርካታ ክለቦች ውስጥ በግብ ጠባቂነት ማገልገል የቻለው ሳዳት ጀማል ወደ ስልጠናው ዓለም ከገባ በኋላ የሀድያ ሆሳዕና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ እንዲሁም የራሱን አካዳሚ በማቋቋም በማሰልጠን ያሳለፈ ሲሆን በቅርቡም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ወልቂጤ አምርቶ የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ለመሆን በቃል ደረጃ ተስማምቶ ስራውን ሲሰራ ቆይቶ በዛሬው ዕለትም በይፋ የቡድኑ ረዳት መሆኑ እንደተረጋገጠ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።