የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ለገጣፎ ለገዳዲ

ለገጣፎ ለገዳዲ የታሪኩን የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ለማድረግ ከወትሮው የአዲስ አዳጊዎች መንገድ የተለየ አቅጣጫን መርጧል።

ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ዕርከን ለማደግ ከፍ ያለ ፉክክር በሚደረግበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከ2009 ጀምሮ ሲፋለም የቆየው ለገጣፎ ለገዳዲ በተለይም በ2011 እና በኮቪድ ምክንያት በተቋረጠው ቀጣዩ የውድድር ዓመት ሊጉን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት ቀርቶ ነበር። 2014 ላይ በሦስት ምድቦች ተከፍሎ በተደረገው ውድድር ግን ሰምሮለት ዘንድሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተታታፊ ሆኗል። በከፍተኛ ሊጉ ‘ምድብ ለ’ ተደልድሎ ውድድሩን ሲያደርግ የነበረው ክለቡ እስከ ፍፃሜው ዕለት በዘለቀው ትንቅንቅ 36 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ከጨረሰው ቤንች ማጂ ቡና በሦስት ነጥቦች በመላቅ ነበር የፕሪምየር ሊጉን ትኬት የቆረጠው።

ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከፍ ሲሉ ቡድናቸውን በአሰልጣኝም ሆነ በተጫዋቾች ሙሉ ለሙሉ ቀይሮ መቅረብ ይቀናቸዋል። ከዚህ አንፃር ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ “የፕሪምየር ሊግ ልምድ” አስፈላጊነት የሚንፀባረቅባቸው ቢሆንም ለገጣፎ ግን የተለየ መንገድን መርጧል። ከዚህም ውስጥ ዘግይቶም ቢሆን የአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመን ውል የማደሱ እርምጃ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። ከአምናው አንፃር የለገጣፎ ለገዳዲ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት አንድ ምክትል አሰልጣኝ እና አንድ የህክምና ባለሙያን በመጨመር ለአዲሱ ፈተና ሲዘጋጅ ሰንብቷል። በዚህም መሰረት ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ በረዳት አሰልጣኝነት ዳዊት ይፍሩ እና ዲሪባ ጃንቦ ፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ፍቃዱ ገብሩ አብረው ሲቀጥሉ አሰልጣኝ እዮብ ዋቤ በረዳት አሰልጣኝነት ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

ከአሰልጣኞች ባለፈ ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ላይ በንፅፅር ያልተጋነነ ተሳትፎን ነበር ያደረገው። በሊጉ የረጅም ዓመታት ልምድ ካካበቱ አልያም በትልቅ ደረጃ ከሚታወቁ እና የብዙ ክለቦች ዓይን አርፎባቸው በዝውውር መስኮቱ ዜና ሆነው ከሰነበቱ ተጫዋቾች ይልቅ ክለቡ አቅሙን ባገናዘበ ሁኔታ ይጠቅሙኛል ያላቸውን ሰባት በሊጉ ከፍ ያለ እና መካከለኛ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። በዚህም መሰረት ዮናስ በርታ ፣ አንተነህ ናደው ፣ የአብቃል ፈረጃ ፣ ጋብርኤል አህመድ ፣ መሐመድ አበራ እና አላዛር ዘውዱ ወደ ለገጣፎ መጥተዋል።

ከዚህ ውጪ ፊቱን ቀድሞ ወደነበረበት ከፍተኛ ሊግ በመመለስ ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ዶጂ ፣ ተከላካዮቹ መሐመድ ሻፊ እና ታዬ ጋሻው፣ አማካዩ ካርሎስ ዳምጠው እንዲሁም አጥቂዎቹ ኢብሳ በፍቃዱ እና ምትኩ ጌታቸውን ማስፈረም ችሏል። በሌላ በኩል ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ፣ ተከላካዮች መዝገቡ ቶላ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ አቤል አየለ ፣ ኪሩቤል ወንድሙ ፣ አማካዮች አንዋር አብዱልጀባል እና ተፈራ አንለይ ከቡድኑ ጋር በፕሪምየር ሊጉ አብረው የሚቀጥሉ ተጫዋቾች ሆነዋል። በሌላ በኩል ፍቅሩ ዓለማየሁ ፣ አበበ ለገሰ ፣ ቴድ ንጉሴ እና ሱራፋል ኪዳኔ የተባሉ ወጣት ተጫዋቾችን በስብስቡ አካቷል።

ይህን መሳይ የነበረው ቡድኑን የማዋቀር ሂደት በአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እይታ ሲገመገም “የምንወዳደረው የሀገሪቷ ትልቅ የሊግ ውድድር ነው። ለዚህ ትልቅ በጀት በጅቶ ትልቅ ተጫዋች ማስፈረም ላይ እንደ ከተማ አስተዳደር የተቀመጠ አቅጣጫ ነበር። ሁሉን ተጫዋቾች ይዘን እንቀጥላለን። ክፍት ባሉ ቦታዎች ላይ ልምድ ያላቸውን ወጣት ተጫዋቾችን እንቀላቅላለን ብለን ነበር። ባሰብነው ልክ የምንፈልጋቸውን ልጆች አግኝተናል ጥሩ ነው።” በሚለው አስተያየታቸው የሚጠቃለል ነው።

ለገጣፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ከረዱት ተጫዋቾች ውል ያላቸውን እንዲሁም ከከፍተኛ ሊጉ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች አጣምሮ መቀጠሉ ሲነሳ አብሮ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ በመሀል የነበረው የዕረፍት ጊዜ ጉዳይ ነው። ቡድኑ የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎውን በድል በደመደመበት እና ለዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ዝግጅት በጀመረበት ቀን መሀል ከአራት ወራት በላይ ማሳለፉ ብዙሀኑን ተጫዋቾች ይዞ ከመቀጠሉ አንፃር ለዘንድሮው ዝግጅቱ ፈተና ተደርጎ ይወሰዳል። በሊጉ ላይ ከቆዩ ቡድኖች ጋር ስናስተያየው የለገጣፎ ተጫዋቾች ከሌሎች ክለቦች ተጫዋቾች አንፃር ከሁለት ወር በላይ ያለውድድር እና ልምምድ አሳልፈዋል። ይህ የጊዜ ርቀት ተጫዋቾች በአካልም ሆነ በአዕምሮ ለአዲስ ውድድር ከመቅረብ አንፃርም ዝግጁነታቸው ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ነው። አሰልጣኝ ጥላሁንም ይህ ክፍተት የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜያቸው ላይ የነበረውን ተፅዕኖ ከተጫዋቾች ዝግጁነት ጋር አያይዘው እንዲህ ይገልፁታል። “አብዛኛው ተጫዋች ከኑሮውም ከአካባቢም አንፃር እንዲሁም ከሜዳ እጥረት ተዘጋጅተው አልመጡም። በግሩፕም በተናጠልም በሚሰራው የአካል ብቃት በሚፈለገው ደረጃ ስላልደረሱ ረጅም ጊዜ ነው የሰራነው። ከተለመደው ውጪ ሩጫዎችን አካሂደናል። ያው ሲመጡ ጉራማይሌ ስለነበሩ ለማስተካከል ጊዜ ፈጅቶብናል።”

ነባሩን ቡድን ይዞ መቀጠሉ ከዝግጅት አንፃር ይህ ፈተና ቢኖረውም ለቡድን ግንባታ ግን የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። አብሮ መቆየት ከሚሰጠው የውህደት ዕድል በተጨማሪ ለገጣፎ ምድቡን በበላይነት አጠናቆ መምጣቱ ምንም እንኳን ወደ አዲስ ባህሪ ወዳለው ውድድር ቢገባም ነባሩ ስብስብ ጥሩ የማሸነፍ ሥነ ልቦናን እና እርስ በእርስ የመተማመን መንፈስን ይዞ እንዲቀርብ ይረዳዋል። ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው በተሳተፈበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ከነባር ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ስብስቡ የዕንግዳነት ስሜት የማይነበብበት እና የበታች ሆኖ ለተጋጣሚው አጨዋወት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በራሱ መንገድ መፎካከርን የመረጠ ሆኖ መታየቱ ይነሳል።

“እኛ ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ ልጆች ናቸው ያሉት። አዳዲስ ያስገባናቸውም አሉ የቡድን መንፈሱን፣ እንዲሁም አብረው የቆዮ መሆናቸው ቡድኑ የተዋሀደ ፣ ተጫዋቾች እርስ በእርስ የተግባቡ ናቸው። ከፍተኛ ሊግ ላይ አሸንፈን ስንመጣ የነበረው ህብረት ነው አሁንም ያለው። የተለያዩ ልጆች ስናስገባ የተለያዩ ፍላጎቶች ስለሚኖር ያንን አጣጥሞ ለመሄድ ከባድ ነው። እኛ ግን የእግርኳስ ግንዛቤያቸው እና ፍላጎታቸው ተመሳሳይ በሆኑ ነባር ተጫዋቾችን ነው ለማቆየት ወስነናል።” የሚለው የአሰልጣኙ አስተያየትም ከላይ ያነሳነውን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው።

ይህን መሳይ የቡድን ግንባታ የተከተለው ለገጣፎ ከነሐሴ 09 ጀምሮ መቀመጫውን በቢሾፍቱ ከተማ በማድረግ በከተማዋ በሚገኘው ለምለም ተስፋ ትምህርት ቤት ሜዳ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ ሰንብቷል። የተጫዋቾችን የአካል ብቃት ደረጃ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ እንዲሁም ቡድኑን በማዋሀድ ሥራ ላይ ያተኮረው ለገጣፎ ራሱን ማየት የቻለባቸውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች አድርጓል። በቢሾፍቱ ከሚገኙ የአንደኛ ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይም አራት ጨዋታዎችን ከውኗል። ከዚህ ባለፈ ለክረምት ውድድር ወደ ሀገራችን ከመጣ የናይጄሪያው ቡድን ጋር እንዲሁ አቋሙን የገመገመበትን ጨዋታ ማድረግ ችሏል። እነዚህ የዝግጅት ጊዜ ጨዋታዎች ሚና በአሰልጣኙ አንደበት እንዲህ ይገለፃል። “ቡድናችንን በየደረጃው አይተናል። መሻሻሎች እና ለውጦች አሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እስካደረግነው ውድድር ድረስ ለውጦች አሉት። የምፈልገውን የልጆቼን መዋሀድ ቋሚ አሰላለፌን ለመስራት ችያለሁ። በአጠቃላይ የአቋም መለኪያው ጨዋታ ውጤቶቹም ጥሩ ስለነበሩ ጥሩ የሞራል ስንቅ ሆኖናል።”

ለገጣፎ ለገዳዲ በፕሪምየር ሊጉ በወጣት አሰልጣኞች ከሚቀርቡ ክለቦች መካከል አንዱ ነው። አምና በከፍተኛ ሊጉ ውድድር መሀል ላይ ከምክትል አሰልጣኝነት ወደ ዋና አሰልጣንኘት ከፍ ያሉት ጥላሁን ተሾመ የሊጉን አዲስ ፈተና ለመጋፈጥ ተዘጋጅተዋል። “እኔ አምና ከነበረኝ ላይ ራሴን አሻሽዬ ማወቅ የሚገባኝን ለማወቅ ጥረት አድርጊያለሁ። እኔ በባህሪዬ መጠየቅ እወዳለው ፤ ከተለያዩ አሰልጣኞች ያለውን ነገር ለመረዳት ችያለው። ትልቅ ሊግ ትልቅ ውድድር ነው። ያሉኝም ልጆች ለዛ ውድድር ተገዢዎች ስለሆኑ የተሻለ ነገር ከፈጣሪ ጋር እናሳያለን።” የሚሉት አሰልጣኙ በሊጉ ለወጣት አሰልጣኞች የሚሰጠውን እምነት ከፍ ከማድረግ እንዲሁም የራሳቸውን በትልቅ ደረጃ የማሰልጠን አቅም ለማሳየት ከቀናት በኋላ የሚጀምረው የሊጉ ውድድር የራሱን ዕድል እና ፈተና ይዞላቸው ይቀርባል።

ለገጣፎ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ እግርኳስ ከሚጫወቱ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀስ ሆኖ ቆይቷል። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እንደታየው ደግሞ ዘንድሮ በቅብብሎች ፈጥኖ ወደ ማጥቂያ ዞን ለመድረስ የሚጥር እንዲሁም የቆሙ ኳሶችን በግብ ምንጭነት የሚጠቀም ዓይነት ባህሪ ተላብሶ ታይቷል። ይህ ቀጥተኝነትን የቀላቀለ አቀራረብ በሊጉ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ ቡድን ሊያደርገው ቢችልም ከስብስቡ አንፃር የሊጉን ከባቢ የመረዳት ደረጃው አንዱ ፈተና ሊሆንበት ይችላል። ለዚህም በቡድኑ ውስጥ ከፍ ያለ ልምድ ያላቸው እንደ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ አማካዩ ጋብርኤል አህመድ ዓይነት ተጫዋቾች ቡድኑ በውድድሩ የተለያዩ ሂደቶች ውስጥ የራሱን ሚዛን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል። ከዚህ ውጪ በዘንድሮው ውድድር ራሳቸውን የማሳየት ዕድል የሚያገኙ ተጫዋቾች ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ በሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ውስን ሚና የነበራቸው መሐመድ አበራ ፣ አንተነህ ናደው እና የአብቃል ፈረጃ ይጠቀሳሉ። በከፍተኛ ሊጉ ግብ አግቢዎች ዝርዝር ውስጥ የማይጠፋው እና አምና በስምንት ግቦች የምድቡ ከፍተኛ ግብ አግቢ የነበረው ኢብሳ በፍቃዱ እንዲሁም በሁለቱ ሊጎች በመጫወት የሚታወቀው ካርሎስ ዳምጠውም በለገጣፎ ቀጣይ ጉዞ ላይ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው ይገመታሉ።

ከከፍተኛ ሊጉ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለው ለገጣፎ የዘንድሮው ዋነኛ ግቡ ራሱን በሊጉ ማቆየት ስለመሆኑ መገመት ይቻላል። ነገር ግን በመጡበት ዓመት የወረዱ እንዳሉ ሁሉ በመጡበት ዓመት ብርቱ ተፎካካሪ የሆኑ እንደ ጅማ አባ ጅፋር እስከ ቻምፒዮንነት የሄደ ቡድንም በሊጉ መታየቱ ለገጣፎ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ያሳየውን ብቃት መቀጠል ከቻለ አንዳች ነገር ሊያሳይ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው። “በአንዴ ለደረጃ እንጫወታለን ብለን አናስብም። የዘንድሮ ዓላማችን ክለቡ ተፎካካሪ ሆኖ በሊጉ እንዲቆይ ነው። በዚህ ዓመት ውድድራችን መሰረት ጥለን በቀጣይ ለማስተካከል ነው። በሊጉ ከወገብ በላይ እንጨርሳለን ብለን እናስባለን።” የሚሉት አሰልጣኝ ጥላሁን ግን ነገሮችን በሂደት የማሳካት እሳቤ እንዳላቸው አስተያየታቸው ይናገራል።

ሶከር ኢትዮጵያ የለገጣፎ ለገዳዲን የዝግጅት ጊዜ ለመቃኘት በቢሾፍቱ ለምለም ተስፋ ትምህርት ቤት ሜዳ በተገኘችበት አጋጣሚ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ በመጨረሻ የሰጡት አስተያየት ይህ ነበር። “ለገጣፎ ለገዳዲ ይህን ዕድል ስላጠኝ አመሰግናለው። ባልተለመደ ሁኔታ ቡድን ከታችኛው ሊግ ያሳደጉ አሰልጣኞች ለፍተው የልፋታቸውን ውጤት ሳያዮ የሚባረሩበት ሁኔታ ነው ያለው። ከተማው ግን ይሄን ዕድል ስለሰጠኝ በጣም አመሰግናለው። ደጋፊዎቼን፣ ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለው።”

ለገጣፎ ለገዳዲ በታሪኩ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደርጋል።

የለገጣፎ ለገዳዲ የ2015 የቡድን ዝርዝርግብ ጠባቂዎች

በሽር ደሊል
ወንድወሰን ገረመው
ሚኪያስ ዶጂ

ተከላካዮች

መዝገቡ ቶላ
አስናቀ ተስፋዬ
ታምራት አየለ
ዮናስ በርታ
በረከት ተሰማ
አንስዋር መሐመድ
ኪሩቤል ወንድሙ
አቤል አየለ
ፍቅሩ ዓለማየሁ

አማካዮች

አንዋር አብዱጀባር
ተፈራ አንለይ
ዳዊት ቀለመወርቅ
ያብቃል ፈረጃ
አንተነህ ናደው
ጋብርኤል አህመድ
ኦካይ ጆሎ
ካሳሁን ሰቦቃ
ሱራፌል ኪዳኔ

አጥቂዎች

ኢብሳ በፍቃዱ
ካርሎስ ዳምጠው
አላዛር ዘውዱ
አቤል ታምራት
መሐመድ  አበራ
ብሩክ ብርሃኑ
አማኑኤል  ኤርቦ
አበበ ለገሰ
ቴዲ ንጉሴ

አሰልጣኞች

ዋና አሰልጣኝ – ጥላሁን ተሾመ
ረዳት አሰልጣኝ – እዮብ ዋቤ
ረዳት አሰልጣኝ – ዳዊት ይፍሩ
ረዳት አሰልጣኝ – ድሪባ ጃንቦ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ – ፍቃዱ ገብሩ
የቡድን መሪ – ኩባ ዘውዴ
የሕክምና ባለሙያዎች – ቢኒያም ተፈራ እና መላኩ ተስፋዬ