ሪፖርት | አስገራሚ ትዕይንቶች የነበሩት ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ኢትዮጵያ መድንን አሸናፊ አድርጓል

አስገራሚ ምልሰቶች የነበሩት የአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት መድንን ባለድል አድርጓል።

በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ አንድ ለምንም የተሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ፍልሚያ ከግማሽ በላይ ለውጦችን አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም አሸናፊ ፊዳ፣ ሙና በቀለ፣ ቡታቃ ሸመና፣ መላኩ ኤሊያስ፣ አቡበከር ሻሚል እና አህመድ ሁሴን የበርናንድ ኦቺንግ፣ አካሉ አትሞ፣ መሪሁን መስቀሌ፣ ሱራፌል ዳንኤል፣ ወርቅይታደስ አበበ እና አሸናፊ ተገኝ ቦታን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። እንደ ተጋጣሚያቸው በመጀመሪያው ሳምንት ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው አሚር ሙደሺር እና ያሬድ ዳርዛን በኪቲካ ጅማ እንዲሁም ቴዎድሮስ በቀለ ለውጠው አስገብተዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ መሪ አግኝቷል። በዚህም አርባምንጭ ከተማ ከወደ ቀኝ ባደላ መስመር ለማጥቃት ሲሞክር ተከላካዮች ያወጡት ኳስ ከመዓዘን ሲሻማ አሸናፊ ፊዳ ሁለተኛውን ኳስ አሸንፎ ግብ አስቆጥሯል። በጊዜ መመራት የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው መጣር ይዘዋል። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድም መንቀሳቀስ የጀመሩ ሲሆን በ13ኛው ደቂቃም አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ከግራ መስመር ከኪቲካ ጅማ እግር የተነሳውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

በጥሩ ደቂቃ ምላሽ የሰጡት መድኖች በ21ኛው ደቂቃ ደግሞ ወደመሪነት ሊሸጋገሩ ነበር። በዚህም ከቅጣት ምት የተነሳውን ኳስ ሀብታሙ ሸዋለም በግንባሩ ሲያሻማው ያገኘው ብሩክ ኳሱን በተቀበለበት ክፍሉ ወደ ግብ ቢልከውም አሸናፊ ፊዳ መክቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ግን ውጥናቸው ሰምሮ ከመመራት ወደ መምራት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ብሩክ በጥሩ እይታ ለኪቲካ አቀብሎት ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ኪቲካ በግራ እግሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

በባህር ዳር ስታዲየም ቀዝቃዛ የዐየር ሁኔታ ቢኖርም አልቢትር እያሱ ፈንቴ የሚመሩት ጨዋታ ግን ሞቅ ያለ ፍክክር እየታየበት ነበር። የጨዋታው ሦስተኛ ግብ ከተቆጠረ ከደቂቃ በኋላም ሌላ ድንቅ ግብ ተስተናግዷል። በዚህም ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ቢጀምሩም ተከታታይ ሁለት ግቦችን ያስተናገዱት አርባምንጭ ከተማዎች ተመስገን ደረሰ በመቀስ ምት ባስቆጠረው ጎል አቻ ሆነዋል።

ከአጋማሹ አካፋይ ሰዓት በኋላ በግብ ሙከራዎች ረገድ ቀዝቀዝ ያለው ጨዋታው ቀጣዩን የግብ ማግባት ሙከራ ለማስተናገድ 10 ደቂቃዎች ወስደውበት ነበር። በ34ኛው ደቂቃም በረጅሙ የተላከውን ኳስ የመድን ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው እግሩ ስር የደረሰው እንዳልካቸው መስፍን ከሳጥኑ ውጪ አክርሮ መትቶት ቁመታሙ የግብ ዘብ አቡበከር ኑሪ አድኖታል። አጋማሹም ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሮ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ምልልሶች እና ግቦች የነበሩበት አልነበረም። ይልቁንም ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ አዘል የኳስ ቁጥጥር ለመያዝ ሲጥሩ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ የወሰዱት አርባምንጭ ከተማዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ዳግም መሪ ለመሆን ሲጥሩ ነበር።

በአጋማሹ እስከ 74ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ባይደረግም በዚህ ደቂቃ ተመስገን በግራ የሳጥኑ ክፍል ሰፊ ቦታ አግኝቶ የአጋማሹን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ጥቃት ሰንዝሯል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ይሁ ተጫዋች ቡድኑን ወደ መሪነት የወሰደች ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ተገኝ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አስጨናቂ ፀጋዬ በወረደ ውሳኔ ሲጨርፈው ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ተመስገን አግኝቶት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከደቂቃ በኋላም ሌላኛው ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤሊያስ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከርን አልፎ በግራ እግሩ ወደ መረብ ልኮት መሪነታቸውን ወደ አራት ለማሳደግ ቢጥሩም ቴዎድሮስ በቀለ ደርሶ ኳስ የግቡን መስመር እንዳታልፍ አድርጓል።

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም እንደ አጀማመሩ ድራማዊ ክስተቶችን በማስተናገድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግቦች በደቂቃ ልዩነት ተቆጥረው ውጤቱ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቷል። በቅድሚያም በ86ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተነሳ ኳስ በሚገባ መፅዳት ሳይችል የተከላካይ አማካዩ አስጨናቂ ፀጋዬ መረብ ላይ አሳርፎት አርባምንጮችን ወደ ጭንቅ ሰዓት ከቷል። የአስጨናቂ ጎል ከፀደቀ ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ በጨዋታው ጥሩ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ኪቲካ ድንቅ ኳስ ተቀይሮ ለገባው ኢዮብ ገብረማርያም አቀብሎት ኢዮብ የማሸነፊያውን ግብ በግራ እግሩ አስቆጥሯል።

ሁለት ጊዜ በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ የተነጠቁት አዞዎቹ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት አማካዩ ኢማኑኤል ላሪዬ ከመስመር አሻምቶ እንዳልካቸው ለመጠቀም ሲጥር አቡበከር ኑራ ከእጁ ምልጦ በተፈጠረ አጋጣሚ አቻ ለመሆን ቢቃረቡም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 4ለ3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አስገራሚ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ያገኙት አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጨዋታው ድራማዊ እንደሆነ ገልፀው እንደዚህ አይነት የመቀዳደም ፉክክር መኖሩ ጥሩ እንደሆነ በማንሳት ተጫዋቾቻቸው ያሳዩትን ተጋድሎ በማድነቅ ከሽንፈት ወደ አሸናፊነት መምጣታቸው ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል። አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪም እንደ ገብረመድኅን ጨዋታው ጎሎች ያሉት እና በፉክክር የተሞላ በመሆኑ አዝናኝ እንደሆነ ጠቅሰው በመጨረሻ ደቂቃ በቡድናቸው ላይ የታየው የትኩረት እና የራስ መተማመን ክፍተት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረው ውጤቱ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።