ሴፋክሲያኖች የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል

በነገው ዕለት ፋሲል ከነማን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የሚገጥመው የቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን በባህርዳር ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል፡፡

በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሁለተኛው ዙር ማጣሪያ መርሐ-ግብር ነገ 10 ሰዓት ፋሲል ከነማን በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም የሚገጥመው የቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን ከወሳኙ ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታው በሚያካሂድበት ሰዓት አከናውነዋል፡፡ ሀያ አምስት ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ ወደ አርባ የሚጠጉ የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ትላንት ረፋድ ባህርዳር የደረሱት ሴፋክሲያኖች በብሉ ናይል አቫንቲ ሆቴል ማረፊያቸውን ካደረጉ በኋላ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን አመሻሽ ላይ በዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ያከናወኑ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በጨዋታው ዋዜማ ቀለል ያለ ልምምድ በባህር ዳር ስታዲየም ሰርተዋል።

በ41 ዓመቱ አሰልጣኝ ካሪም ዳልሆም የሚመሩት ሴፋክሲያኖች በልምምዳቸው ወቅት ቀለል ያሉ የኳስ ስራዎች እንዲሁም የአካል ብቃት እና ቦታ አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠናን በተለያዩ የቡድኑ አሰልጣኞች ሲከውኑ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ መታዘብ ችላለች፡፡

ስለነገው ጨዋታ ከቡድኑ አምበል እና ማነጀር ጋር ያደረግነውን ቆይታ ደግሞ በቀጣይ የምናቀርብ ይሆናል።