ሽመልስ በቀለ ወደሌላኛው የግብፅ ክለብ ተዘዋውሯል

ከኤል ጎውና ጋር ያለው ውል የተጠናቀቀው የዋልያዎቹ አምበል ሽመልስ በቀለ ሌላ አዲስ ክለብ ተቀላቅሏል።

ከስምንት ዓመታት በፊት ፔትሮጀትን በመቀላቀል የግብፅን እግርኳስ የተዋወቀው ሽመልስ በቀለ በክለቡ ለስድስት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ሌላኛውን የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለል መቃሳን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን ዓምና በመቃሳ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም በስምምነት ተለያይቶ የኤል ጎውናን መለያ በመልበስ በሊጉ ሲጫወት ነበር። ኤል ጎውና በግብፅ ሊግ የተሳካ ቆይታን ሳያደርግ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የወረደ ሲሆን ሽመልስም ከክለቡ ጋር ያለው ውል በመጠናቀቁ ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ንግግር ሲያደርግ ቆይቷል።

አሁን የግብፅ ብዙሃን መገናኛዎች ይፋ ባደረጉት መረጃ መሠረት ሽመልስ በቀለ በነፃ ዝውውር በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 9ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኤንፒ’ን በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል።

ከዚህ ቀደም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ዑመድ ኡኩሪ በኤንፒ ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወሳል።