መረጃዎች | 16ኛ የጨዋታ ቀን

አራተኛ የጨዋታ ሳምንት ፍፃሜውን የሚያገኝባቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ተሰናድተዋል።

ፋሲል ከነማ ከ መቻል

በጨዋታ ሳምንቱ ከሚደረጉ ጨዋታዎች የተሻለ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የምሳ ሰዓት ጨዋታ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያሳየናል ተብሎ ይጠበቃል።

በአህጉራዊ ውድድር ምክንያት ሁለት የሊግ መርሃግብራቸው ወደ ሌላ ጊዜ በመዘዋወሩ መነሻነት ከሌሎች ቡድኖች በተለየ ሁለተኛ የሊግ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ፋሲል ከነማዎች ሊጉ አዳማን በመርታት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከቱኒዚያው ሃያል ክለብ ሴፋክሲያን ጋር በደርሶ መልስ ብርቱ ፉክክር ቢያደርጉም በጠባብ ውጤት ተሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን ከነገው ጨዋታ ጀምሮ በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጋር ከባድ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው ሲሆን ከወዲሁ በሰንጠረዡ አናት አካባቢ ለመገኘት ውጤቶቹን አጥብቆ ይሻል።

በአዲሱ የውድድር ዘመን በአዲስ ስያሜ እና በአዲስ ስብስብ የቀረቡት መቻሎች አጀማመራቸው አመርቂ አልሆነላቸውም። ከሦስት ጨዋታዎች ባሳኩት ብቸኛ የመክፈቻ ዕለት ድል ቡድኑ በሰንጠረዡ ከወገብ በታች ይገኛል።

በሊጉ በመጀመሪያ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በድምሩ በአስራ ስድስት አጋጣሚዎች ከጨዋታ ውጭ በሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጫዋቾቻቸው በመገኘታቸው ማጥቃታቸው የተቋረጠባቸው መቻሎች በዚህ ረገድ በሊጉ ቀዳሚ የመሆናቸው ጉዳይ ስለቡድኑ የማጥቃት ድክመት ዓይነተኛ ማሳያ ነው።በተለይ ሽንፈት ባስተናገዱባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በቅድሚያ ግቦችን ማስተናገዳቸውን ተከትሎ የቡድኑ ማጥቃት ከብስለት ይልቅ ከልክ ባለፈ ጉጉት የሚዘወር መሆኑ ቡድኑ ላይ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ ያሳያል።

በመቻሎች በኩል ቶማስ ስምረቱ እና ኢብራሂም ሁሴን አገልግሎት የማያገኙ ሲሆን በፋሲል ከነማዎች በኩል ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት እንዲሁም ሽመክት ጉግሳ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ ግልጋሎት አይሰጡም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለዘጠኝ ጊዜያት የተገኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በአምስቱ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው።

ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ተካልኝ ለማ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ፋሲካ የኋላሸት እና ወጋየሁ አየለ በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው ተመድበዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ በሆነው መርሃግብር መነቃቃት ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያ መድንን የመጀመሪያ ድሉን ፍለጋ ላይ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።

ኢትዮጵያ መድኖች ከመጀመሪያው ጨዋታ አሰቃቂ ሽንፈት ማግስት ባደረጓቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥቦችን በማሳካት ከአስደንጋጩ ሽንፈት ማግስት እያንሰራሩ ይገኛል። ከማሸነፋቸውም ባለፈ በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ አራት ግቦችን እያስቆጠሩ ማሸነፍ መቻላቸው በአውንታዊነት የሚነሳ ጉዳይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ እስካሁን በሊጉ ያስቆጠራቸው ዘጠኝ ግቦች በሰባት ተጫዋቾች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ከሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል በርከት ባሉ ተጫዋቾች ግቦች ያስቆጠረ ቡድን መሆኑ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት የሚገመት ስላለመሆኑ ማሳያ ነው።

ከዚህ ባለፈ በሊጉ እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች አራት ለግብ የሆኑ ኳሶችን በመስጠት ቀዳሚው ተጫዋች የሆነው ወጣቱ ኪቲካ ጅማ ከሰሞነኛው የቡድኑ መነቃቃት በተለይም በማጥቃቱ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተወጣ ይገኛል። አንድ ግብ በስሙ ማስመዝገብ የቻለው ወጣቱ ኪቲካ በግራ መስመር ሆነ ከአጥቂ ጀርባ እየተገኘ የቡድኑን ማጥቃት በአስደናቂ ብቃት እየዘወረ ይገኛል።

በሊጉ እስካሁን ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የፈፀሙት ወላይታ ድቻዎች እንደ አምናው ሁሉ በህብረት በትጋት የሚከላከል ቡድን ቢሆንም አሁንም ግን በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ ብዙ የሚያስፈራ ቡድን ሆኖ አልተመለከትነውም። በሁለት ጨዋታዎች አምስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን አሁንም ቡድኑ ማጥቃቱ ከመዋቅር ይልቅ በግለሰቦች መልካም የጨዋታ ቀን ማሳለፍ ላይ የተመሰረተ የመሆኑ ጉዳይ ስጋት የሚያጭር ነው።

በጣም ጠጣር በሆነ መከላከል ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የተወሰነ የጨዋታ ቅፅበቶችን የሚጠባበቀው ቡድኑ አዲስ ፈራሚያቸው በሀይሉ ተሻገር ይህ ሂደት በማሳለጥ ረገድ ሚናውን ማሳደግ የሚጠበቅበት ሲሆን ከእሱ ባለፈ ለቡድኑ ከኳስ ጋር የተሻለ ተስፋን ሲፈነጥቅ እየተመለከትነው የሚገኘው ወጣቱ አበባየሁ አጪሶም እንቅስቃሴ ለቡድን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በወላይታ ድቻዎች በኩል የግብ ዘቡን ፂሆን መርዕድን ጨምሮ እንድሪስ ሰዒድ እና ቢኒያም ፍቅሬ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በአንፃሩ በኢትዮጵያ መድን በኩል ደግሞ ፀጋሰው ድማሞ እና ተካልኝ ደጀኔ በጉዳት ነገም በተከላካይ መስመራቸው አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን ዩጋንዳዊው አጥቂ መጠነኛ መሻሻሎችን ቢያሳይም በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር እስካሁን አለየለትም።

ይህን ጨዋታ ዮናስ ካሳሁን በመሀል ዳኝነት ፣ አበራ አብርደው እና ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት ሲመሩት ባህሩ ተካ ደግሞ ለጨዋታው በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።