ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዓመቱ የመጀመሪያ ድል አሳክቷል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች ለገጣፎ ለገዳዲን 3-0 አሸንፏል።

ኢትዮ ኤሌክልትክ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪ አድርገዋል፡በዚህም ሙሴ ካበላ እና አላዛር ሽመልስን በማስወጣት ምንያህል ተሾመ እና ሔኖክ አየለን ወደ ቋሚ አሰላለፍ አካተዋል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ከገጠማቸው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለገጣፎ ለገዳዲዎች በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በለውጦቹ ወንድወሰን ገረመው ፣ ዳዊት ቀለመወርቅ ፣ አቤል አየለ እና ተፈራ አንለይ ወጥተው በሽር ደሊል ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ ታምራት አየለ እና አማኑኤል አረቦ ተተክተዋል።

ፈጥን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሻለ አቅም በታየበት በቀዳሚው አጋማሽ ጨዋታው በጀመረ ሁለተኛ ደቂቃ ላይ አማካዩ አብነት ደምሴ ከግቡ ትይዩ ከፀጋ ደርቤ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ መትቶ በሽር ደሊል በቀላሉ ይዞበታል፡፡ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ወደ ፊት ለመሳብ በሚያስቡበት ወቅት የትኩረት ማዕከላቸውን አጥቂው ካርሎስ ዳምጠው ላይ አድርገው ቢንቀሳቀሱም ብልጫ የነበራቸው ግን የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ናቸው፡፡ መሀል ለመሀል እና በመስመሮች በኩል አልፎ አልፎ ደግሞ በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ትጋቶች ያልተለያቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እንዳሳዩት ጥረትም ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል፡፡

22ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ በቀለ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ወደ ለገጣፎ የግራ የግቡ አቅጣጫ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሔኖክ አየለ ወደ ሳጥን ውስጥ ገፋ ካደረገ በኋላ በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

የለገጣፎን ደካማ የጨዋታ አቀራረብን በደንብ ለመጠቀም ቶሎ ቶሎ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች 25ኛው ደቂቃ ላይ መዝገቡ ቶላ ፀጋ ደርቤ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ አልቢትር ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ሔኖክ አየለ ቢመታም በሽር ደሊል መልሶበታል። ሆኖም 29ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው ዋለጬ ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተገኘውን የቅጣት ምት አብነት ደምሴ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት አክርሮ በመምታት ሁለተኛ ግብ አድርጎታል፡፡

ብሩክ ብርሀኑ በመልሶ ማጥቃት ካደረጋት ሙከራ ውጪ ሸሽተው አብዛኛውን ደቂቃዎች ያሳለፉትን ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሌላ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 44ኛ ደቂቃ ላይ ጌቱ ኃይለማርያም ከቀኝ የለገጣፎ የግብ አቅጣጫ የተገኘን የቅጣት ምት ሲያሻማ የለገጣፎ ተከላካዮች ኳስን በአግባቡ ማራቅ ባለመቻላቸው አንጋፋው አማካይ ምንያህል ተሾመ እግሩ ስር የገባችውን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሯት በ3-0 በሆነ ውጤት ወደ ዕረፍት ወጥተዋል፡፡

ከመልበሻ ቤት ሲመለስ ጨዋታው አሁንም የኳስ ቁጥጥር ድርሻው ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ልክ እንደ መጀመሪያው አርባ አምስት ሁሉ ያዘነበለ ነበር፡፡ በአንፃሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ለገጣፎ ለገዳዲዎች ኳስን ለመቆጣጠር የሚመስል የተጫዋች ለውጥን አድርገዋል፡፡ ያብቃል ፈረጃ ፣ ተፈራ አንለይ እና መሐመድ አበራን አከታትለው ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በዚህም ቅያሪ መነሻነት በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት አዲስ አዳጊው ክለብ ደካማ የአጥቂ ክፍልን መያዛቸው የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፈላቸው መስሏል፡፡ መሐመድ አበራ ካደረጋት ሙከራ ውጪ ሙከራ ለማድረግ ረጅም ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ኪሩቤል ወንድሙ ሲመታ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ የያዘበት አጋጣሚ ተጠቃሿ ሙከራ ነበረች፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች አብዛኛዎቹን የጥቃት መሰንዘሪያቸውን ወደ ግራ አቅጣጫ በፀጋ ደርቤ አማካኝነት በማጋደል ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመንቀሳቀስ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የታየባቸው የግብ ዕድልን የመፍጠር ክፍተት ተጨማሪ ጎሎች እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 ድል አድራጊነት ነበረች፡፡

የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጨዋታውን መቆጣጠራቸውን እንዲሁም ባሰቡት ልክ መሳካቱን ገልፀው ከፍተኛ ሞራል ያለውን እና በመከላከልም የተሻለውን ቡድን ማሸነፍ መቻላቸውን ጨምረው ከገለፁ በኋላ ቡድናቸው ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሉንም አክለዋል፡፡ የተሸናፊው ለገጣፎ አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ጥሩ በተጫወተው ቡድን መሸነፋቸውን አምነው በልምድ ችግር እና በተከላካዮች ትኩረት ማጣት ጎሎች እንደተቆጠረባቸው እና አጥቂዎቻቸውም ደካማ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡