ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አግኝቷል

የአራተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ስብስብ ላይ ባደረጉት ለውጥ አንተነህ ጉግሳን በደጉ ደበበ ብቻ ሲተኩ በአንፃሩ ኢትዮጵያ መድኖች ደግሞ ለገጣፎ ለገዳዲን ከረታው ስብስብ ሳይለውጡ በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

የጎል ዕድል በመፍጠር ረገድ እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ከባለፈው ከመጡበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ወጥተው ከዚህ ጨዋታ አንዳች ነገር ለማድረግ የማጥቃት ፍላጎትን አሳይተዋል። ሆኖም ግን ጥረታቸው ከቆሙ ኳሶች ብቻ መሆኑ ፍሬያማ መሆን ሳይችል ቀርተዋል። በተከታታይ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በመጠኑም በመሐል ሜዳ ላይ ቀዝቀዝ ብልው የታዩት መድኖች በቅጡ የተሳካ ቅብብል ማድረግ ተስኗቸው የሚቆራረጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ባሲሩ ኡመር ያሻገረለትን ኪቲካ ጅማ በደረቱ ኳሱን አውርዶ በመምታት ካመከነው ውጭ የጠራ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ብሩክ ሙልጌታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ቢመታውም ግብ ጠባቂው ቢንያም ወደ ጎልነት እንዳይቀየር አድኖታል። ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ በዚህ የውድድር ዓመት በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናው ብሩክ በየነን ፍፁም ቅጣት ምት ማዳኑ ይታወሳል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ መንገድ በተጠና መንገድ ጎል ለማግኘት የሚደረጉት ቅብብሎች ስኬታማ መሆን በለመቻላቸው ደካማ የጎል ሙከራ ለማየት ተችሏል። 67ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ መድን በኩል ከቀኝ መስመር አብዱልከሪም መሐመድ ያሻገረውን ተቀይሮ የገባው ሲሞን ፒተር በግንባሩ የገጨውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበት የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ኢትዮጵያ መድኖች በ71ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ብቸኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። በመልሶ ማጥቃት ባሲሩ ዑመር የጀመረውን ብሩክ ሙሉጌታ ተቀብሎ ከግራ መስመር ያሻገረውን ባሲሩ ሳጥን ውስጥ ደርሶ በግንባሩ አመቻችቶ ያቀበለውን ሲሞን ፒተርም በግንባሩ በመግጨት ጎሉን አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩ ቀሪ ደቂቃዎች መድኖች ወላይታ ድቻዎች ጥለውት የሚሄዱትን ክፍት ሜዳ በመጠቀም ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩ ቢመስልም በሂደት ግን ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት መከላከሉ ላይ አመዝነው ታይተዋል። ወደ ጨዋታው ለመግባት ጎል ፍለጋ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተደጋጋሚ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ድቻዎች ተቀይሮ በገባው ዮናታን አልያስ ከቅጣት ምት የፈጠረው አጋጣሚን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪ እንደምንም ካዳነበት ዕድል ውጪ ጥረታቸው ይሄን ያህል አስፈሪ አልነበረም። በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከመጀመርያው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ በተከታታይ ጨዋታ እየተሻሻሉ የመጡት የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የመጨረሻው አስራ አምስት ደቂቃ ውጤቱን ከመፈለግ የተነሳ ራሳቸውን ጫና ውስጥ ከተው እንደነበረ ተናግረው ከመጀመርያው ጅማሮ አንስተው ኳሱን በስርዓት በመቆጣጠር የነበራቸው ብልጫ ለውጤቱ መገኘት አስተዋፆኦ እንደነበረው ገልፀዋል። አክለውም የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው አዲስ ፈራሚዎቻቸው ወደ ሜዳ መግባትት በቡድኑ ውስጥ ትልቅ ሚና እየተወጡ እንዳሉ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን አውስተዋል።

በውድድር ዓመቱ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የተቸገሩት
የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ጨዋታው ተመጣጣኝ እንደነበረ ከሌላው ጊዜ ቡድናቸው የተሻለ ቢሆንም ውጤት ቀያሪ የሚባሉ የጎል ዕድሎችን በመጠቀም በኩል እንደተቸገሩ ተናግረው ከዚህ በኋላ በአጨራረስ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።