ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ወደ ሱዳን ተጉዘዋል

በሱዳን አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት ዋንጫ ጨዋታ ላይ በዳኝነት ግልጋሎት ለመስጠት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡

በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግርኳስ ተቋም በሆነው (ሴካፋ) አዘጋጅነት ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በሱዳን አስተናጋጅነት ካርቱም ላይ ይከናወናል፡፡ ሰባት ሀገራትን በተሳታፊነት የሚያቅፈው ውድድሩ ቀደም ብሎ ከተቀመጠለት ቀን በአንድ ሳምንት ተራዝሞ የፊታችን ዕርብ ጥቅምት 18 እንደሚጀምር ከቀናቶች በፊት በዘገባችን መጠቆማችን የሚታወስ ሲሆን የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው ሴካፋ በዞኑ ካሉ ሀገራት ውድድሩን በዳኝነት እንዲመሩ ሲመርጥ ለሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ጥሪ በማስተላለፉ ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን በባህርዳር ከተማ በዳኝነት ሲመሩ ከነበሩ ኢንተርናሽናል ዳኞች መካከል በዋና ዳኝነት ኃይለየሱስ ባዘዘው በረዳት ዳኝነት ተመስገን ሳሙኤል ጥሪው ደርሷቸው ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡

በውድድሩ በምድብ ሀ – ጅቡቲ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሱዳን እና ብሩንዲ ሲደለደሉ በምድብ ለ – ዩጋንዳ ፣ ታንዛኒያ እና ሀገራችን ኢትዮጵያ ተደልድለዋል፡፡