መረጃዎች | 19ኛ የጨዋታ ቀን

የአምስተኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ነገ በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚውል ሲሆን እኛም ሁለቱን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን አቅርበናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

የሦስተኛ የጨዋታ ቀን የመክፈቻ መርሃግብር ባለ ሜዳውን ባህር ዳር ከተማን ከአዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ የሚያገናኝ ይሆናል።

የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን ከጨዋታ ጨዋታ እያሳደጉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ከኳሱ ባለፈ ግን ጨዋታን በመቆጣጠር ረገድ ግን አሁንም በሚፈለገው ደረጃ አይገኙም። በዚህም ጥሩ በመሰሉባቸው ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብን ይዘው ለመውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ዘግይተው ቡድኑን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በሁሉም የሜዳ ክፍሎች እስካሁን ተቀዳሚ ተመራጮቻቸውን ያገኙ አይመስልም። ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከረቱበት የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አሰልጣኙ በድምሩ አስር የመጀመሪያ አስራ አንድ ተጫዋቾች ለውጥን አድርገዋል።

ምንም እንኳን አሰልጣኙ ምርጡን አስራ አንድ እየፈለጉ ቢገኝም ቡድኑ ዘንድሮም እንደ ባለፉት ጊዜያት በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ታጅቦ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በሚፈለገው ደረጃ ውጤት መያዝ እየቻለ አይገኝም። በመሆኑም ቢያንስ በከተማው የሚያደርገውን ቆይታ በሙሉ ሦስት ነጥብ ለመደምደም በነገው እና በቅዳሜው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ከቡድኑ ደጋፊው ብዙ ይጠብቃል።

ጉዳት ላይ የነበሩት አጥቂዎቹ ኦሲ ማውሊ እና አደም አባስ እንዲሁም በግል ጉዳይ ባለፈው ጨዋታ ያልነበረው አማካዩ የዓብስራ ተስፋዬ ለነገው ጨዋታ ለምርጫ ዝግጁ ሲሆኑ በመጀመሪያ ጨዋታ ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ጨምሮ ተስፋዬ ታምራት እና ፍፁም ጥላሁን ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በሊጉ ጥሩ አጀማመርን ማድረግ ችለው የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን የሊጉ እውነተኛ ፈተናን መጋፈጥ የጀመሩ ይመስላል። በተከታታይ ባደረጓቸው ሁለቱ ጨዋታዎች አብረዋቸው ከታችኛው ሊግ ባደጉት ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድምሩ ሰባት ግቦችን አስተናግደው የመሸነፋቸው ነገር ለአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እና ስብስባቸው የማንቂያ ደውል ይመስላል። በመሆኑም ቡድናቸው በፍጥነት ወደ ውጤታማነት ለመመለስ በባህር ዳሩ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በግሩም የህብረት ጨዋታ ነጥቦችን መያዝ ችለው የነበሩት ለገጣፎዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች መጠነኛ መቀዛቀዝ የተመለከትንባቸው ሲሆን ከነገውም ጨዋታ አውንታዊ ውጤት ይዘው ለመውጣት ያንን የህብረት ጨዋታ መመለስ ይጠበቅባቸዋል። በለገጣፎዎች በኩል ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የቆየው ዮናስ በርታ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር ግን አጠራጣሪ ነው።

በትልቁ የሊግ እርከን ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘውን ይህን የምሳ ሰዓት ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት አሸብር ታፈሰ እና ወጋየሁ አየለ በረዳትነት እንዲሁም ዳንኤል ግርማይ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው ተመድበዋል፡፡

መቻል ከ ኢትዮጵያ መድን

አስደናቂ ሰሞነኛ ግስጋሴ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በሚያደርጉት በዚሁ ጨዋታ ይህን ግስጋሴያቸውን ለማስቀጠል ፋሲልን በማሸነፍ ወደ ድል ከተመለሰው መቻል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በውጤትም ሆነ በጨዋታ መንገድ የተጠበቁትን ያህል ለመሆን የተቸገሩት መቻሎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን ሲረቱ ኳሱን ለተጋጣሚያቸው በመተው በጠንካራ መከላከል እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ያደረጋቸው ሲሆን በጨዋታውም በውድድሩ ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በክፍት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር መቻላቸውም እንዲሁ በመልካምነት የሚነሳ ነው።

በነገው ጨዋታ ከፋሲሉ ጨዋታ አንፃር ይበልጥ አውንታዊ ሆኖ እንደሚጫወት የሚጠበቀው የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ መቻል ቶማስ ስምረቱን ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ሲሆን ኢብራሂም ሁሴን ግን በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ታውቋል።

ሁለተናዊ የመሻሻል ፍንጮችን እየሰጡ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች አሁን ላይ መልካም አየርን መተንፈስ ጀምረዋል። እንደ ቡድን መነቃቃት ላይ የሚገኘው መድን በተለይ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች መሰለፍ ሳይችሉ ቀርተው የነበሩት ጋናዊው አማካይ ባሲሩ ዑመር እና ዩጋንዳዊው አጥቂ ፒተር ሳይመን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ ላይ እየፈጠሩ የሚገኙት ተፅዕኖ እጅግ አስደናቂ ነው። ሁለቱም ከወዲሁ በስማቸው አንድ አንድ ግብን ያስመዘገቡ ሲሆን በድቻው ጨዋታ ሳይመን ያስቆጠራትን ግብ ባሲሩ አመቻችቶ ማቀበሉ ቡድኑ በቀጣይም ሁለቱ ተጫዋቾች ይበልጥ ሊጉን እና ቡድኑን ሲላመዱ ከዚህ በላይ ቡድኑን ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ነው።

በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሚመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በነገው ጨዋታ የተከላካዮቻቸው ተካልኝ ደጀኔ እና ፀጋሰው ድማሙን አገልግሎት በጉዳት እንዲሁም ጋናዊው ተከላካይ ሀቢብ መሀመድ የወረቀት ሥራዎች እስከ አሁን ባለማለቃቸው የማያገኙ ሲሆን የተቀሩት ተጫዋቾች ግን ለምርጫ ዝግጁ መሆናቸውን ማወቅ ችለናል።

ሁለት ከድል የተመለሱትን ቡድኖች የሚያገናኘውን የ10 ሰዓት ጨዋታ ዮናስ ካሳሁን በመሀል ዳኝነት እንዲሚመሩት ሲጠበቅ ሙሉነህ በዳዳ እና ታምሩ አደም በረዳትነት እንደሁም ደግሞ ባህሩ ተካ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ያገለግላሉ፡፡