ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ5ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ5ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአንፃራዊ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-2-3-1

ግብ ጠባቂ


በረከት አማረ – ኢትዮጵያ ቡና

ያለፉትን 270 ደቂቃዎች ግቡን ያላስደፈረው በረከት አልፎ አልፎ ጥቃቅን ስህተቶችን ቢሰራም ቡድኑን ከሽንፈት የሚጠብቅበት መንገድ የሚደነቅ ነው። በአርባምንጩም ጨዋታ አራት ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ያዳነ ሲሆን በምቾት ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ የሚያቀብልበት መንገድም ተጫዋቹ ከግብ ዘብነት ባለፈ ከኳስ ጋር ምቾት እንዳለው ያስመሰክራል።

ተከላካዮች


አብዱልከሪም መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን

ከጨዋታ ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴን እያደረገ የሚገኘው አብዱልከሪም መሐመድ በቀኝ ተከላካይ ቦታ ተቀዳሚ ምርጫችን አድርገነዋል። ተጫዋቹ በቦታው ኳሶችን የሚያቋርጥበት መንገድ እና ቡድኑ በሚያጠቃ ጊዜ ወደ ፊት በመሄድ ከመስመር የተለያዩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሁም ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት በሚጠቃ ሰዓት በፍጥነት ቦታውን በመሸፈን ኢትዮጵያ መድን ወሳኙን ድል መቻል ላይ እንዲያገኝ ትልቁን ሚና ተወጥቷል።

አስቻለው ታመነ – ፋሲል ከነማ

የዐፄዎቹ አምበል አስቻለው ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ እጅ እንዳይሰጥ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ በከፍተኛ መታተር ሲጫወት አስተውለናል። በዋናነት ደግሞ የሊጉ እና የፈረሰኞቹ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በምቾት ኳሶችን እንዳይጠቀም ሲያደርግ የነበረበት መንገድ እና አጠቃላይ የተከላካይ ክፍሉን የመራበት ሂደት ያለ ከልካይ በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል።

ኩዋኩ ዱሃ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ካስቻሉት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ኩዋኩ ዱሃ በአርባምንጩ ፍልሚያ በግሉ ምርጥ ጊዜን አሳልፏል። በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ጠንካራ ሆኖ የታየው ዱሃ ወደ መስመር ተጠግቶም ተሻጋሪ ኳሶችን በማቋረጥ እና ከኋላ በመመስረት ተደራጅቶ የመውጣት አጨዋወትን ለሚከተለው ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ እፎይታ የሰጠ ተጫዋች ሆኗል።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በማጥቃቱ ረገድ የተገደበ ሚና የነበረው አምሳሉ ጥላሁን በመከላከሉ ረገድ ግን ፍፁም የተዋጣለት ነበር። ፈጣኖቹን የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተጫዋቾችን በሚገባ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን ጨምሮ ለቀረበው ቡድኑ ወሳኝም የመከላከል አበርክቶ ነበረው።

አማካዮች


ይሁን እንደሻው – ፋሲል ከነማ

ፋሲሎች በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በሜዳው የላይኛው ክፍል ጫና ለመፍጠር አምስት ተጫዋቾች ወደ ፊት በማስጠጋት ለመጫወት መምረጣቸውን ተከትሎ ከተከላካዮች ፊት በብቸኝነት የተሰለፈው ይሁን እንደሻው በፋሲል አደረጃጀት መሀል የሚገቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ በመገንዘብ ያቋርጥበት የነበረው መንገድ አስደናቂ ነበር ፤ ከዚህ ባለፈ በኳስ ምስረታ እና ማጥቃት ላይ የነበረውን ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን

ይህ ጋናዊው አማካይ ወደ ኢትዮጵያ መድን ከመጣ ወዲህ ገና በሦስት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፎ ቢያደርግም እጅግ አስደናቂ አጀማመር እያደረገ ይገኛል። ለሊጉም ሆነ ለቡድኑ አዲስ የሆነው ተጫዋቹ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር በፍጥነት በማስተካከል ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። ከጥልቅ የሚነሳው አማካዩ በመከላከል ሆነ በማጥቃት ወቅት የሚገኝባቸው ቦታዎች እጅግ አስገራሚ ናቸው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛውን ግብ ማግኘት የቻለው ተጫዋቹ በመድን ቤት አስደናቂ ብቃቱን ማሳየት ቀጥሏል።

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

ከቅጣት በተመለሰበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሽመክት ጉግሳ ከኳስ ጋር ሆነ ያለ ኳስ የነበረው አበርክቶ ጥሩ የሚባል ነበር። ከኳስ ውጪ በመታተር የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ላይ ጫና ሲያሳድር የነበረው ሽመክት ከኳስ ጋር ደግሞ በጨዋታው አስፈሪ የነበረውን የቡድኑን የቀኝ መስመር ማጥቃት ከመዘወር ባለፈ በጨዋታው ልዮነት የፈጠረችውን የታፈሰ ሰለሞንንም ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ታፈሰ ሰለሞን – ፋሲል ከነማ

ወደ ፋሲል ከነማ ካመራ በኋላ ከቀደመው ሚናው በተለየ ይበልጥ ወደ ፊት ተጠግቶ እየተጫወተ የሚገኘው ታፈሰ ሰለሞን ከአዲሱ ሚናው ጋር በሚገባ እየተላመደ ይገኛል። ባልተለመደ መልኩ ከኳስ ውጭ ጫና ለማሳደር ተነሳሽነት እየተመለከትንበት የምንገኘው ታፈሰ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ወሳኟን ግብ ከሳጥን ውጭ ከማስቆጠረ ባለፈ ከፍ ብለው የመከላከል ዕቅድን ተግባራዊ ለማድረግ ባለመው የቡድኑ ዕቅድ ውስጥ ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል።

አደም አባስ – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ለገጣፎ ለገዳዲን እንዲረታ ሜዳ ላይ በቆየባቸው 70 ደቂቃዎች የተቻለውን ሲያደርግ የነበረው አደም ፉዐድ እና ማውሊ ያስቆጠሯቸውን ሁለት ኳሶች የግል ብቃቱን ተጠቅሞ አመቻችቶ አቀብሏል። በተለይ ሁለተኛው ጎል ሲገኝ ኳስ ነጥቆ ረዘም ያለ ሜትር በመግፋት ራሱን ለጉዳት አጋልጦ ያቀበለው ኳስ ብዙዎች እንዲያደንቁት አድርጓል።

አጥቂ


ቢኒያም ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

ከዓምናው በተሻለ ዘንድሮ የመሰለፍ ዕድል እያገኘ የሚገኘው ቢኒያም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከጎል ጋር ተገናኝቷል። ምንም እንኳን ቡድኑ ቢኒያም ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ባያስጠብቅም ተጫዋቹ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት የሀዋሳን ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ተወጥቶ ወጥቷል ፤ ይህንን ተከትሎ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል።

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በድል የተወጡት የዐፄዎቹ አሰልጣኝ የሳምንቱ ኮከባችን ሆነዋን። ከጨዋታው ተጠባቂነት እንዲሁም ተጋጣሚያቸው ከነበረበት ወቅታዊ አቋም አንፃር ሙሉ ነጥብ ማሳካታቸው አሰልጣኙን ያስመረጣቸው ሲሆን ቡድናቸው በርካታ ግቦችን ሲያስቆጥር የቆየውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ምንጮች ያደረቀበት እና መሪነቱን አስጠብቆ የወጣበት መንገድ ደግሞ ከሳምንቱ ተፎካካሪዎቻቸው ልቀው እንዲገኙ ምክንያት ሆኗል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑራ
ዳንኤል ደምሱ
ዓለምብርሃን ይግዛው
አብነት ደምሴ
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን
ራምኬል ሎክ
እንዳለ ከበደ
ብሩክ በየነ