መረጃዎች | 33ኛ የጨዋታ ቀን

የ9ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ድሬዳዋ ከተማ

ጥሩ የሆነ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የ10 ሰዓቱ ጨዋታ በብዙሃኑ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።

በ18 ነጥቦች በሊጉ ዛሬ ከተጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በዕኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጠው በ2ኛ ደረጃ እየመሩ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች እስካሁን በሊጉ ካስተናገዷቸው ሁለት ሽንፈቶች ውጪ በተቀሩት ስድስት ጨዋታዎችን ባለድል ናቸው። እንደ ባህር ዳር ቆይታቸው ሁሉ የድሬዳዋ ቆይታቸውን በሽንፈት ቢጀምሩም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ተጋጣሚዎቻቸውን መርታት ችለዋል።

ከመጀመሪያው ጨዋታ ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከመዘናቸው ኢትዮጵያ መድኖች በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ እጅግ አስደናቂ መሻሻሎችን እያሳዩ የሚገኙ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ጅማሮ በሊጉ ለመቆየት ያስቀመጡትን ግብ ለማሳካት በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ ይገኛሉ።

20 ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ አሁንም ግቦችን ከተለያዩ ተጫዋቾች ማግኘቱን ቀጥሏል። በመጨረሻ ጨዋታቸው ሲዳማ ቡናን ሲረቱ ዮናስ ገረመው ግብ ማስቆጠሩን ተከትሎ በውድድር ዘመኑ ለመድን ግብ ያስቆጠረ 10ኛ ተጫዋች ሲሆን ይህም ቁጥሩ የቡድኑ ማጥቃት ከተለያዩ ተጫዋቾች እንዴት ግቦችን እያገኘ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።ነገሮች ሁሉ በትክክለኛ ጉዳና እየተጓዙለት የሚመስለው ቡድኑ ነገ በሜዳው እና በደጋፊው ከሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚገጥመው ይጠበቃል።

በነገው ጨዋታ ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከራቀው የመስመር ተከላካያቸው ሳሙኤል ዮሐንስ ውጭ ኢትዮጵያ መድኖች በተሟላ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ወደ መቀመጫ ከተማቸው ከተመለሱ ወዲህ ወደ ቀልባቸው የተመለሱ የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በደጋፊያቸው ፊት ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን በማሳካት በሰንጠረዡ ሽቅብ መጓዛቸውን ቀጥለው አሁን ላይ በ11 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የአሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባዩ ስብስብ ምንም እንኳን በጨዋታዎች ፈጥን ያለ አጀማመርን ለማድረግ ቢቸገርም በተለይ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ግን የሚያሳዩት አዎንታዊ ምላሽ ግን ጥሩ የሚባል ነው። በመሆኑም ቡድን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጨዋታዎችን የሚጀምርበትን መንገድ ማጤን ይኖርበታል።

በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ትኩረቶች በሙሉ አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው ላይ ያረፉ ቢመስሉም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከአዲስ አበባ ከተማ ድሬዳዋን የተቀላቀለው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ሰሞነኛ ብቃት ግን እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ፍፁም በሆነ መሰጠት እየተጫወተ የሚገኘው አሰጋኸኝ በተለይ የተጋጣሚን የማጥቃት ሂደት በወሳኝ ሰዓት የሚያቋርጥበት መንገድ ለቡድኑ መከላከል ቁልፍ ሚና እንዲወጣ እያስቻለው ይገኛል።

በነገው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል እንየው ካሳሁን በቅጣት አሁንም የማይኖር ሲሆን የመስመር አጥቂው አቤል ከበደ በህመም የነገው ጨዋታ የሚያልፈው መሆኑ ተረጋግጧል። በመጨረሻው ጨዋታ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው ሙኸዲን ሙሳም በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር ሲያጠራጥር በተመሳሳይ ከኤሌክትሪኩ ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ በልምምድ ወቅት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አቤል አሰበ ግን አገግሞ ለነገው ጨዋታ የሚደርስ ይሆናል።

ድሬዳዋ እና መድን ከዚህ ቀደም 4 የግንኙነት ታሪክ ሲኖራቸው አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው ሁለት ጊዜ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። እኩል ሁለት ሁለት ግብም አስቆጥረዋል።

ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ድልን አጥብቀው የሚናፍቁትን ሁለቱን የርዕሰ መዲናዋን ክለቦች የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታ ሽንፈትን ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአምስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ተከትሎ ዛሬ ረፋድ ወደ ሊጉ ካሳደጋቸው እና የመውጫ በሩ ላይ ከሰነበቱት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር የመለያየታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል።

ቡድኑ ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ቢያስተናግዱም በጨዋታው የነበራቸው ፍላጎት እና ትጋት አስገራሚ ነበር ከዚህ ባለፈም በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ ለመግደል የሚያስችሏቸውን ዕድሎችን ቢያገኙም መጠቀም ያለመቻላቸው በስተመጨረሻ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

መጠኑ ይለያይ እንጂ ኤሌክትሪኮች በሊጉ ዘንድሮ ያደረጓቸው አብዛኞቹ ጨዋታ በተመሳሳይ መገለፅ የሚችሉ መሆናቸው በጊዜያዊነት በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እየተመሩ የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉት ኤሌክትሪኮች አሁንም ወደ ተቃናው መንገድ ለመመለስ ሩቅ ስላለመሆናቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል። መወገድ የሚችሉ የመከላከል ስህተቶችን ማስወገድ ሆነ የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ መሻሻሎችን ካሳዩ አሁንም ቢሆን ቡድኑ ካለበት ስፍራ ቀና ማለታቸው የሚቀር አይመስልም።

ወጥ የሆነ ብቃትን ከጨዋታ ጨዋታ ለማሳየት የተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ድሬዳዋ አምርተው ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ፍፁም ደካማ ከነበረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር በድምሩ ስድስት ግቦችን አስተናግደው የተሸነፉ ሲሆን ይህን ተከትሎ በ10 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በመከላከሉ ረገድ በቀላሉ ተጋላጭ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየታየ የሚገኘው ቡድኑ እንደ ቡድን ከኳስ ውጭ በተደራጀ መልኩ ከመከላከል አንፃር ወስንነቶች ያሉበት ሲሆን በተከላካይ መስመራቸው ላይ ደግሞ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ክዌኩ ዱሃ ደግሞ በግሉ በተከታታይ ጨዋታዎች እየሰራቸው የሚገኙ ስህተቶች ቡድኑን ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛል።

በሊጉ ደረጃ አሉ የተባሉ ተስፈኛ አጥቂዎችን ሆነ የአጥቂ አማካዮቹን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያሰባሰበው ቡድን እስካሁን ድረስ ለእነዚህ ተጫዋቾች የተመቸ መዋቅር በመፈለግ ላይ ያለ ይመስላል። በአማካይ በጨዋታ አንድ ግብ ብቻ እያስቆጠረ የሚገኘው ቡና ከግለሰባዊ ቅፅበቶች ባለፈ የቡድኑ የመፍጠር አቅም በጣም ደካማ ከመሆኑ ባለፈ የጨዋታ መንገዱ የአጥቂዎቹን በተለይ ጥልቀትን ለማጥቃት የተመቹ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት መቃኘት ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ቡና በነገው ጨዋታ ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከነበሩት አስራት ቱንጆ እና መስፍን ታፈሰ በተጨማሪ በባህር ዳሩ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደውን አምበላቸው አማኑኤል ዮሀንስንም ግልጋሎት አያገኙም። በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በነገው ጨዋታ የምንያህል ተሾመ እና አላዛር ሽመልስን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ40 ጊዜያት ተገናኝተው ቡና 21 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት እዟል። 10 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 9 ጊዜ  አቻ ተለያይተዋል። ቡና 68 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 43 አስቆጥሯል።

የምሽቱን ጨዋታ ሄኖክ አክሊሉ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል።