ሪፖርት | ነብሮቹ ቡናማዎቹን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ የግሉ አድርጓል።

ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ሁለት አቻ ተለያይተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በለውጦቹም ኩዋኩ ዱሀ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ገዛኸኝ ደሳለኝ አርፈው አንተነህ ተፈራ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ እና ሔኖክ ድልቢ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ሆኗል። በባህር ዳር ከተማ የሁለት ለምንም ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በዚህም በሔኖክ አርፊጮ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና አክሊሉ ዋለልኝ ምትክ ካሌብ በየነ፣ ግርማ በቀለ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎ በቀዳሚው አሰላለፍ ተካተዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያስተናገደው በ6ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃም ሔኖክ ድልቢ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ከግቡ አግዳሚ ጋር ተባብሮ ሲያወጣው ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ደግሞ የመዓዘን ምት ሆኖ ሲሻማ ጫላ ተሽታ በግንባሩ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል። ቡናዎች ይህንን ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ቢሆንም ቀጣዩን ጥቃት ለመሰንዘር ግን 37 ደቂቃዎችን መጠበቅ አስፈልጓቸዋል።

የቡናን የኳስ ቅብብል በራሳቸው ሜዳ እያጨናገፉ በፈጣን ሽግግር ወደ ላይኛው ክልል መድረስን የመረጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሩብ ሰዓት በራሳቸው በኩል የመጀመሪያውን ግልፅ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ለቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የነበረው ቃሌብ በየነ ያሻማውን የቅጣት ምት ግርማ በቀለ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በ22ኛው ደቂቃ ደግሞ በግራ መስመር ሰመረ ሀፍታይ ይዞ የገባውን ኳስ ሲያሻማው በተቃራኒ ቋሚ የነበረው ፀጋዬ ብርሃኑ ወደ ግብ ልኮት ዒላማውን ስቶበታል።

በመጠኑ ጫና የበዛባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በ33ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ዳግም ንጉሴ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲልከው በወረደ የጊዜ አጠባበቅ ኳሱን ለመመለስ የወጣው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ተሳስቶ ኳሱን ወደ ግቡ በመጭረፍ ግብ ተቆጥሮ ሀዲያ መሪ ሆኗል።

ቡናማዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ባገኙት የቅጣት ምት አቻ ለመሆን ቢሞክሩም የግቡ ቋሚ እና ተከላካዮች ውጥናቸውን አምክነውባቸዋል።

የአሠልጣኝ ተመስገን ዳና ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃም መሐመድኑር ናስር ከግራ መስመር ኃይለሚካኤል አደፍርስ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ለማግባት ዳድቶ ግብ ጠባቂው ጥቃቱን ከመስመር ላይ አምክኖበታል። በ59ኛው ደቂቃ ደግሞ ብሩክ በየነ ከተቃራኒ አቅጣጫ ሔኖክ ድልቢ የላከውን ኳስ በተመሳሳይ በግንባሩ መረብ ላይ ለማሳረፍ ሞክሮ ተመልሷል።

ከኳስ ውጪ ጨዋታን መቆጣጠር ላይ የተጠመዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አልፎ አልፎ ብቻ በመልሶ ማጥቃት የቡና የመከላከል ሲሶ ቢደርሱም በዚህ አጋማሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ አጋጣሚ የፈጠሩት በ71ኛው ደቂቃ ነበር። ከመዓዘን ምት የተሻማን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት ዳግም በተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ወጥቶ ፀጋዬ የደረሰውን ኳስ በግንባሩ ቢመታውም ቋሚው ጋር ቆሞ የነበረው አብዱልሀፊዝ ከግብነት ታድጎታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በሌላ የቆመ ኳሰ ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ሰንዝረው መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀሪ ደቂቃዎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት የአቅማቸውን ቢጥሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተው እጅ ሰጥተዋል። ጨዋታውም በሀዲያ አንድ ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።