የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ፣ ቦሌ እና መቻል ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ5ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሦስት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ቀጥለው ሲከወኑ አዳማ ከተማ ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና መቻል በተጋጣሚያቸው ላይ ድልን የተቀናጁበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ረፋድ 4 ሰዓት ሲል አዳማ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው ነበር፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የአዳማ ከተማ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ተሽሎ መገኘት የቻለበት የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ በፈጠሩት ጫናም 14ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩዋ ሳባ ኃይለሚካኤል ከርቀት አክርራ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ ኳስን ይዞ ለመጫወት ሲጥሩ ይታይ እንጂ ወደ ሦስተኛው የአዳማ የግብ ክልል ገብቶ ዕድልን ለመፍጠር የተሳናቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች 26ኛ ደቂቃ ሔለን እሸቱ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ከመረብ ባሳረፈችው ልዩነቱን ወደ ሁለት አሳድገዋል፡፡

39ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ደግሞ ሦስተኛ ግብን ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉን ተሻሽሎ መቅረብ የቻለው የአሰልጣኝ ራውዳ ዓሊው ቡድን በእየሩስ ወንድሙ አማካኝነት ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ጨዋታው በአዳማ 3-2 የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈችው እየሩስ ወንድሙ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የመዲናይቱ ክለቦች የሆኑትን ልደታ ክፍለ ከተማን እና ቦሌ ክፍለ ከተማን አገናኝቶ የተካሄደ ነበር፡፡ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን ባስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር ከእንቅስቃሴ ውጪ የግብ ዕድሎችን መመልከት እንድንችል ያላስቻለን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ከ85ኛው ደቂቃ በኋላ በተወሰነ መልኩ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የጣሩት ቦሌ ክፍለ ከተማዎች በተከላካዮች ስህተት 90ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን አጋጣሚ ተቀይራ የገባችው አስቴር ደግአረገ አስቆጥራው ቡድኗን መሪ አድርጋ ጨዋታውም ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለቦሌ ክፍለ ከተማ የመከላከል ጉልበትን ያላበሰችው ሒሩት ብርሀኑ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡

የሳምንቱ የማሳረጊያ በሆነው የመቻል እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርን አሳይቶን በመጨረሻም በመቻሎች አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው በሁለቱም አጋማሾች ጠንካራ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅርቃሴን ያየንበት ሲሆን ከዕረፍት መልስ በተለይ ከአጋማሹ በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉት መቻሎች ተሳክቶላቸው አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ 70ኛው እና 83ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ የግል አቅሟን የተጠቀመችባቸውን ሁለት ግቦች ለቡድኗ አስቆጥራ መቻል 2ለ0 አሸናፊ ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የግቦቹ ባለቤት ሴናፍ ዋቁማ የጨዋታው ድንቅ በመባል ተሸልማለች፡፡