ከፍተኛ ሊግ | የ2ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

በሦስቱ አዘጋጅ ከተሞች ስምንት ጨዋታዎች በተስተናገዱበት የከፍተኛ ሊጉ የዛሬ ውሎ ሀላባ ከተማ ፣ ወልዲያ ፣ ንብ እና ደሴ ከተማ ድል አድርገዋል።

የ04:00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ ባህርዳር ላይ ሀላባ ከተማን ከዱራሜ ከተማ ሲያገናኝ የሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ ለመባል እጅግ ብዙ ምክንያቶች ነበሩት። የበዙ አካላዊ ንክኪዎች ያልነበሩበት እና በማራኪ የኳስ ቅብብል ታግዞ ከጠሩ የግብ ዕድሎች ጋር ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ፉክክርን አስተናግዷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል ሀላባዎች ብልጫውን መውሰድ ሲችሉ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተለይም 42ኛው ደቂቃ በቀኙ የሜዳ ክፍል የነበረው ምስጋና ግርማ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ፎሳ ሰዲቦ ሲያቀብል ፎሳ በጠበበው የግቡ ቋሚ በኩል ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብጠባቂው ማፐቱ ይስሃቅ በእግሩ የመለሰው ኳስ በሀላባዎች በኩል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ፉክክሩ ይበልጥ ደምቆ ሲቀጥል ዱራሜ ከተማዎችም ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው ለጨዋታው ቀርበዋል። የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራም 48ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ወንድማገኝ ኢያሱ ከቀኝ መስመር ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በርበሬዎቹ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ወደግራው የሜዳ ክፍል ካደላ ቦታ ላይ የነበረው በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው አቡሽ ደርቤ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው የማዕዘን ምት አድርጎታል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ዱራሜዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በዚህም ኪሩቤል ካሣ በግራ መስመር ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ለወንድማገኝ ኢያሱ አመቻችቶ ሲያቀብል ወንድማገኝ ያደረገውን ሙከራ በቀኑ እጅግ የተሳካ ጊዜ ያሳለፈው የሀላባው ግብ ጠባቂ ስንታየሁ ታምራት በሚገርም ብቃት መልሶበታል። ጨዋታው በደቂቃዎች ልዩነት ከማራኪ እንቅስቃሴ ጋር በርካታ ሙከራዎች እየተደረጉበት ሲቀጥሉ 77ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። 

በጨዋታው በተለይም ከዕረፍት መልስ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው የዱራሜው አልይታ ማርቆስ ከረጅም ርቀት የተገኘን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ በድኑን መሪ ማድረግ ሲችል መሪነታቸው ግን ከሁለት ደቂቃዎች በላይ አልተጓዘም የሀላባው ሙሉቀን ተሾመ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ትልቅ የግብ አጋጣሚ ሲያገኙ አቡሽ ደርቤ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሙሉቀን ተሾመ ያደረገውን ሙከራ ከሽንፈት ባይታደጋቸውም በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው የዱራሜው ግብ ጠባቂ ማፐቱ ይስሃቅ በሚገርም ፍጥነት አድኖበታል። በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ሀላባዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ ማሸነፊያ ግብ ሲያስቆጥሩ ሙሉቀን ተሾመ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጀሚል ታምሬ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል ጨዋታውም በሀላባ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ከፋ ቡና እና ከንባታ ሺንሺቾን ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ዳዊት ተፈራ ከንባታ ሺንሺቾን 50ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ቢያደርግም ዮናታን ከበደ ከሀያ ደቂቃዎች በኋላ ከፋ ቡናን ነጥብ ያጋራች ጎል አስቆጥሯል።

በምድብ ‘ሐ’ ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የነገሌ አርሲ እና የኦሜድላ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ አልተቆጠረም። በነጌሌ አርሲ በኩል ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ለማድረግ ሲጥሩ በኦሜድላ በኩል ተደጋጋሚ ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተመልክተናል። ከዕረፍት መልስም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የነጌሌ አርሲ የበላይነት የታየበት ጨዋታ ሲሆን ኦሜድላዎች ትኩረታቸውን መከላከል ላይ ሲያደርጉ ታይቷል። በዚሁ ሂደት ነጌሌዎች ሲፈጥሩ የነበሩትን ጫና ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ሊጠናቀቅ ችሏል።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉት ተጫዋቾች ውስጥ በ አርሲ ነጌሌ በኩል የአማካኝ ስፍራ ተጫዋቾቹ እና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች የሆኑት ፍቅሩ ጴጥሮስ ፣ አብርሀም በቀለ፣ አብዱላኪም ሱልጣን እና በመከላከሉ በኩልም ምንተስኖት ተስፋዬ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አጥቂያቸው አብዱላኪም ሱልጣን አንጋፋ እና ልምድ ያለው ተጫዋችነቱን ሜዳ ላይ ሲያሳይ ተመልክተናል።  የኦሜድላን የኋላ መስመር ሰብረው ለመግባት ሲጥሩ እንደነበር ተሰተውሏል። በኦሜድላ በኩል የተከላካይ መስመሩ ቻላቸው ቤዛ እና ተመስገን ታሪኩ ከአርሲ ነጌሌ አጥቂዎች ሲሰነዘር የነበረውን ጫና በመቋቋም ቡድናቸው አንድ ነጥብ እንዲጋራ በዋነኝነት ከረዱት ውስጥ ናቸው።

የ08:00 ጨዋታዎች

በምድብ ‘ሀ’ የተደረገው የወሎ ኮምቦልቻ እና የወልዲያ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ሲደረግ የተጠበቀውን ያህል አዝናኝ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ በድሩ ኑርሁሴን 33ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ብቻ የተሻለው የጠራ የግብ ዕድል ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ተስፋዬ ከግራ መስመር ወደ ግብ ሞክሮት የላዩን አግዳሚ ታክኮ የወጣበት ኳስ በኮምቦልቻዎች በኩል የተሻለ የግብ ሙከራ ሆኖ አጋማሹ ተጠናቋል። ጨዋታው ከዕረፍት መልስ የተሻለ ሆኖ ሲቀጥል 66ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በድሩ ኑርሁሴን አስቆጥሮ ወልዲያን መሪ ማድረግ ችሏል። 

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ኮምቦልቻዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ብሩክ ብርሃኑ ሲሳይ አቡሌ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሽመክት ግርማ ሲመታ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቴዎድሮስ ጌትነት መልሶበታል። ከአምስት  ደቂቃዎች በኋላም ወልዲያ ቢንያም ጥዑመልሳን ባስቆጠረው ግብ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል። ኮምቦልቻዎች በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ለባዶ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሳሙኤል በለጠ ከ ሄኖክ ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው በሚገርም ቅልጥፍና አውጥቶበታል። ጨዋታውም በወልዲያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ንብ እንደ አዲስ ከተመሰረተ በኋላ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል። ቡድኑ ተጋጣሚው ይርጋጨፌ ቡና ላይ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ፉአድ ተማም ፣ ኪም ላም ፣ ንስሀ ታፈሰ ፣ ከፍያለው ካስትሮ እና ከነዓን በድሉ አስቆጣሪዎቹ ነበሩ። ሥዩም ደስታ እና ፋንታሁን ተስፋዬ ደግሞ ይርጋጨፌን ከሽንፈት ያልታደጉ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሆሳዕና ላይ ደሴ ከተማን ከቡራዩ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ለአይን ሳቢ እና ፈጣን እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል የታየበት ነበር ። በቡራዩ ከተማ በኩል መጠነኛ የሆነ የማጥቃት ሙከራ ያሳዩ ቢሆንም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ነበር። በአንፃሩ በደሴ ከተማ በኩል ሲያደርጉት የነበረውን ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ተከትሎ ጨዋታው ወደ ውረፍት ሊያመራ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የአማካኝ ቦታ ተጫዋቹ ተስሏች ሳይመን ድንቅ ግብ በማግባት ደሴ ከተማን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አርጓል። 

ከዕረፍት መልስም ደሴ ከተማዎች የጨዋታ የበላይነታቸውን የወሰዱ ሲሆን ቡራዩ ከተማም አልፎ አልፎ የሚፈጥራቸው የግብ ሙከራ ዕድሎች ነበሩ። በ62ኛው ደቂቃ ላይ የደሴ ከተማው አጥቂ ማናዬ ፋንቱ  ከቡራዩ ከተማ ፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ክልል ውጪ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ ማስቆጠር ችሏል። ግቧም ደሴ ከተማን ሁለት ለባዶ መሪ ያደረገች ሆናለች። ጨዋታውም በዚሁ በመጠናቀቁ ደሴ ከተማ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አግኝቷል።

ጨዋታው ላይ አመርቂ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ተጫዋቾች መካከል በደሴ ከተማ በኩል ማናዬ ፋንቱ የቡራዩን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ በመረበሽ ግብም ማስቆጠር ችሏል። ተስሏች ሳይመን መሀል ሜዳውን ብልጫ በመውሰድ እና ድንቅ ግብም በማስቆጠር እና በድሉ መርዕድም ለደሴ ከተማ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል። በጨዋታው ከፍተኛ የሆነ የደሴ ደጋፊዎች ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውለዋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ የሁለተኛው ሳምንት ማገባደጃ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቡታጅራ ከተማ መካከል ሲደረግ ንግድ ባንኮች ጨዋታው በጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዚህም እንዳለ ዘውገ በግሩም ሁኔታ የሞከረውን ኳስ የቡታጅራው ግብጠባቂ ምንተስኖት የግሌ በሚገርም ብቃት ሊያስወጣው ችሏል። ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ሲችሉ 40ኛው ደቂቃ ላይ ልዑልሰገድ አስፋው ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካደላ ቦታ ላይ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው እና የግቡ የቀኙ ቋሚ ግብ ከመሆን አስቀርተውታል።

 ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 54ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ሀይከር ዱዋሙ ያደረገው የግብ ሙከራ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ቡታጅራዎች በተረጋጋ መንፈስ ጨዋታውን ለማስቀጠል ሲጥሩ ግብ ለማስቆጠር የጓጉት ንግድ ባንኮች ከግብ ክልላቸው ተረጋግተው ለመውጣት ተቸግረዋል። የቡታጅራው የመስመር ተጫዋች ምንተስኖት ዮሴፍ በግሉ በርካታ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በተከናወነው የመጨረሻ ጨዋታ ስድስት ግቦች ተቆጥረዋል። 3-3 በተቋጨው ጨዋታ ጅንካ ከተማ በራስ ላይ በተቆጠረ ግብ እንዲሁም በተመስገን ሀንቆ እና ሴፉ ድሪባ ሲያስቆጥር አዲስ አበባ ከተማ በኤርምያስ ኃይሉ ፣ ዘርዓይ ገብረስላሴ እና ሙሉቀን ታሪኩ ግቦች ነጥብ ተጋርቷል።