ረፖርት | ከድል መልስ የተገናኙት ሀዲያ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

የ12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተደምድሟል።

ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለምንም የረቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግርማ በቀለ እና ፀጋዬ ብርሃኑን በስቴቨን ኒያርኮ እና ራምኬል ሎክ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ገጣፎ ለገዳዲን ሦስት ለምንም ካሸነፉበት ፍልሚያ ዳዋ ሁቴሳን ብቻ በአሜ መሐመድ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በ13 ደቂቃ ውስጥ ሦስት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው በጊዜ መሪ ሊሆኑ ነበር። በቅድሚያ በ11ኛው ደቂቃ አሜ የሳጥኑ ቀኝ ክፍል ላይ ተገኝቶ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርግ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ደስታ ዮሐንስ ከቅጣት ምት ሌላ አጋጣሚ ፈጥሯል። በሦስተኛው አጋጣሚ የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ሀዲያን ፈትነው ተመልሰዋል።

በመጠኑ ጫናዎች የበዛባቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀጥተኛ አጨዋወትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ አዳማ ሳጥን ለመሄድ ቢያስቡም ግልፅ የግብ ዕድል በቀላሉ ሊፈጠርላቸው አልቻለም። ይባስ ብሎ በ33ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር አጥቂው አቡበከር ወንድሙ በሞከረው ጥብቅ ኳስ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አዳማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ባህሩ የጭማሪ ደቂቃ ሲያሳዩ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥረው ነበር። በዚህም በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሀዲያ ሳጥን ይዘውት የሄዱትን ኳስ ዊሊያም ሰለሞን ከአማኑኤል ጎበና ተቀብሎ ቢመታውም የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ ተቆጣጥሮታል።

ሁለተኛውንም አጋማሽ በአዎንታዊ መንገድ የጀመሩት አዳማዎች በ50ኛው እና 51ኛው ደቂቃ ለግብ ቀርበው ነበር። በቅድሚያ ዊሊያም ሰለሞን ሳጥኑ መግቢያ ላይ ሆኖ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ሰይዶ ሲመለስ ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ደግሞ ከመዓዘን ምት ሲሻማ አሜ በግንባሩ ለመጠቀም ሞክሮ ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታል። አሁንም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መጓዝ ያላቆሙት አዳማዎች በ63ኛው ደቂቃ ዳግም ንጉሴ ጥፋት ሰርቶ በተገኘ የቅጣት ምት ቀዳሚ ሊሆኑ ቢሞክሩም ኳስ የግቡን የውጪ መረብ ገጭታ ወደ ውጪ ወጥታለች።

ሀዲያዎች በአጋማሹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ ያደረጉት በ70ኛው ደቂቃ ነበር። ከመዓዘን ምት የተሻማ ኳስ በሚገባ መፅዳት ሳይችል ቀርቶ ራምኬል ሎክ ግብ ሊያደርገው ጥሮ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ በሊጉ ሁለተኛ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ ካሌብ በየነ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ አድርጎ የመታው ኳስ ሰዒድ ሀብታሙ ከግብነት ታድጎታል። ብዙም ሳቢ ያልነበረው ጨዋታው በቀሪ ደቂቃዎች ሌላ ሙከራ ሳይደረግበት ያለ ግብ ፍፃሜውን ቢያገኝም በጭማሪው ደቂቃ አዳማ ግብ ሊያገኝ እጅግ ተቃርቦ ነበር።