ዳዋ ሆቴሳ በቀጣይ ጨዋታዎች ከሜዳ ይርቃል

ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ ጉዳት ላይ የሚገኘው የአዳማ ከተማው ወሳኝ አጥቂ በመጪዎቹ ጨዋታዎችም እንደማይሰለፍ ተረጋግጧል።

በአሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በዘንድሮ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11 ጨዋታዎችን ከውኖ 11 ነጥቦችን በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በእነዚህ ጨዋታዎች በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት ሲያጣ የነበረው ቡድኑ አሁን ደግሞ ወሳኝ አጥቂው ዳዋ ሆቴሳን በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች እንደማያገኝ ታውቋል።

ዳዋ ቡድኑ በ10ኛ ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን ሦስት ለምንም ሲረታ ጉዳት ደርሶበት በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ በአሜ መሐመድ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ጉዳቱም ከጉልበት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተመላክቷል። ምንም እንኳን ጉዳቱ ያን ያህል አሳሳቢ ባይሆንም ተጫዋቹ ወደ አዳማ ተጉዞ የኤም አር አይ ምርመራ ተደርጎለት እረፍት እንደሚያስፈልገው እንደተነገረው ለማወቅ ተችሏል። ይህንን ተከትሎ ተጫዋቹ ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወት ግልጋሎት የማይሰጥ ይሆናል።