ባህር ዳር ከተማ ቅሬታውን አሰምቷል

ባህር ዳር ከተማ ከዳኝነት ጋር በተገናኘ ያለውን ቅሬታ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስገብቷል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በድሬዳዋ ስታዲየም እየተከወነ የሚገኝ ሲሆን የ12 ሳምንት ጨዋታዎችም ከትናንት በስትያ ጀምረዋል። በጨዋታ ሳምንቱ ትናንት የተደረገው የሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ፍልሚያ አንድ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን በጨዋታው በጭማሪ ደቂቃ ግብ ያስተናገዱት ባህር ዳሮችም ለሊጉ የበላይ አካል የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት የጣና ሞገዶቹ በፃፉት ደብዳቤ የዕለቱ ዳኛ ባህሩ ተካ ከጨመሩት 5 ደቂቃ በላይ አራት ደቂቃዎችን ገፍተው አጫውተው አመቺ ቦታ ቅጣት ምት በመስጠት ቡድኑ ውጤት እንዲያጣ አድርገዋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከስፖርታዊ ጨዋታነት ውጪ የተደረገው አካባቢያዊ የዳኝነት ምደባው ልክ አለመሆኑን ጠቅሰው አክሲዮን ማኅበሩ ጉዳዩን አይቶ ውጤቱ እንዲስተካከል እንዲያደርግ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴም ከዳኞች ምደባ ጋር ገለልተኛ ሥራ ይስራ ሲሉ አሳስበዋል።