መረጃዎች | 46ኛ የጨዋታ ቀን

የ12ኛው ሳምንት መቋጫ የሆኑትን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ፋሲል ከነማ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከድል እና ከሽንፈት የተመለሱትን መድን እና ፋሲልን ከ2000ው የውድድር ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊግ የእርስ በእርስ ጨዋታቸው ያገናኛል። ጥሩ የውድድር ዓመት አጀማመር አድርጎ የነበረው ኢትዮጵያ መድን ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘበትን ያለፉት ሳምንታት ደካማ አካሄድ ወልቂጤ ከተማን በረታበት ጨዋታ ማስተካከል ችሏል። ፋሲል ከተማ በተቃራኒው በወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት ገጥሞት 9ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የነገውን ጨዋታ ያደርጋል። ይህ ጨዋታ መድንን በ25 ነጥቦች ወደ አንደኝነት ደረጃ የሚመልሰው ሲሆን ለፋሲል ደግሞ ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ ፉክክሩ የሚያስጠጋው ነው።

ኢትዮጵያ መድን ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመለስ የአሠልጣኙ ጨዋታን አንብቦ ተጫዋች የመቀየር ብቃት ወሳኝ ነበር። የተጋጣሚን ክፍተት የተንተራሰ ለውጥ አድርገው ሲያሸንፉ በማመቻቸትም ሆነ ጎል በማስቆጠሩ ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ሚናቸውን ተወጥተዋል። ይህም ተመሳሳይ ውሳኔዎች በነገው ጨዋታ ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው።

ፋሲል ከነማዎች ከዚህ ቀድም ባልተለመደ መልኩ በወላይታ ድቻውም ሆነ በድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ ከፍተኛ የተነሳሽነት ችግር ታይቶባቸዋል። በመጨረሻው የድሬዳዋ ጨዋታ ቡድኑ በቶሎ ግብ ቢያስቆጥርም ጎሉ ተነሳሽነቱን ሊጨምርለት ባለመቻሉ የግብ ዕድል መፍጠር የከበደው ቡድን ሆኖ ሲታይ በመከላከሉ ረገድም ለተጋጣሚው ተጋላጭ ሆኖ ታይቷል። በመሆኑም አፄዎቹ በነገው ጨዋታ በዋነኝነት የጨዋታ ተነሳሽነታቸውን ከፍ አድረገው መግባት ይጠበቅባቸዋል።

በጨዋታው የፋሲል ከነማው ሀብታሙ ተከስተ እና የኢትዮጵያ መድኑ ሳሙኤል ዮሐንስ ብቻ ቡድኖቻቸውን የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ፣ አዲሶቹ ረዳት ዳኞች ዘመኑ ሲሳይነው እና ደስታ ጉራቻን በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይህንን ጨዋታ ይመሩታል፡፡

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ አርባምንጭ ከተማ

ሁለተኛው የዕለቱ ጨዋታ በሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል ላይ የሚገኙ ተጋጣሚዎች የሚፋለሙበት ነው። ከቀናት በፊት በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ለውጦችን ያደረገው እና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን የቀጠረው ለገጣፎ ለገዳዲ ብቸኛ ድሉን ካስተናገደ ዘጠኝ ጨዋታዎች አልፈዋል። ከመጨረሻው የቡና ሽንፈቱ በኋላ ሦስት አቻዎችን አስመዝግቦ የነበረው አርባምንጭ ከተማ ደግሞ አዳማን በመርታት ከድል ጋር ቢታረቅም በመጨረሻ ጨዋታው ከኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ወደመጋራቱ ተመለልሷል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለገጣፎ ለገዳዲን በዋና አሰልጣኝነት መያዛቸው እርግጥ ቢሆንም የወረቀት ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው ቡድኑ ነገም በአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ መሪነት ጨዋታውን ያደርጋል። በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በጥሩ የቡድን መዋቅር የመሻሻል ተስፋ አሳይቶ የነበረው ለገጣፎ በአዳማ ከተማ ሽንፈት ሲያስተናግድ በድጋሚ ድክመቱ አገርሽቶ ታይቷል። የነገው ጨዋታ የአሰልጣኝ ሹም ሽሩ በቡድኑ መንፈሱ ላይ የሚፈጥረው አንዳች ልዩነት የሚኖር ከሆነ የሚታይበትም ነው።

አርባምንጭ ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ቀደም ብሎ ያሳየውን መልካም አቋም ያጣበትን የመጨረሻ ጨዋታ አድርጎ ነው ለነገው ፍልሚያ የሚቀርበው። ከኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱም እጅግ ተዳክሞ ታይቷል። በተለይ ቡድኑ የሚታወቅበት ከኳስ ውጪ ያለ እንቅስቃሴ እና ቀጥተኛ አጨዋወት መጉላት አልቻለም። ሆኖም በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከሽንፈት መዳኑ በነገው ጨዋታ ወደ ቀደመ መልኩ ለመመልስ የተሻለ መንፈስ እንደሚፈጥርለት ይታመናል።

በጨዋታው ለገጣፎ ለገዳዲ ዮናስ በርታ እና አቤል አየለ ከጉዳት ሲመለሱለት የአርባምንጭ ከተማ ስብስብም ሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል።

ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው ባሪሶ ባላንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ፣ ተከተል በቀለ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ  ጎ ሰብስቤ ጥላዬ በረዳትነት ፣ ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ለዚህ ጨዋታ ተመድበዋል።