መረጃዎች | 47ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 13ኛ ሳምንት መርሃግብር ነገ ጅማሮውን የሚያገኝባቸውን ሁለት መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎቹ በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ መቻል

የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃግብር ከአቻ የተመለሱትን ባህር ዳር ከተማን ከመቻል ለሙሉ ሦስት ነጥብ ያፋልማል።

በሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ባህር ዳር ከተማዎች በሰንጠረዡ በ22 ነጥብ ከመሪው ኢትዮጵያ መድን በአንድ ነጥብ አንሰው 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የጣና ሞገዶቹ ከተከታታይ አራት ድሎች ማግስት በመጨረሻ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ የተጋሩ ሲሆን በሁለቱም ጨዋታዎች በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከጨዋታ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ሲቸገሩ ተመልክተናል።ይህም በሲዳማ ቡናው ጨዋታ አነጋጋሪ በነበረ መንገድ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ እንዲያስተናግዱ ያስገደደ ሲሆን ይህም ባህር ዳሮች የጨዋታ ቁጥጥራቸውን በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ማሻሻል እንደሚገባቸው ጠቋሚ ነው።

አሁንም ቢሆን አስደናቂ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆነው ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ግን በተወሰነ መልኩ ተገማች እየሆነ የመጣ ይመስላል። በመስመር ተጫዋቾቹ ፍጥነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለው የቡድኑ ማጥቃት ተጋጣሚዎች ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እያደረጉ መምጣታቸውን ተከትሎ በተወሰነ መልኩ ሲቸገሩ እያስተዋልን እንገኛለን።

ባህር ዳር ከተማዎች በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ፋሲል አስማማው እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ውጪ የተቀረው ስብስባቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት እጅግ ከናፈቁት ድል ጋር ከስድስት ጨዋታዎች በኃላ የታረቁት መቻሎች ይህን የአሸናፊነት መንፈስ ያስቀጥላሉ ተብለው በተጠበቁበት የመጨረሻ ጨዋታቸው ከወልቂጤ ከተማ ጋር በመጨረሻ ደቂቃ ባገኟት ግብ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።በሰንጠረዡ መቻሎች አሁን ላይ ከ12 ጨዋታዎች በኋላ በ13 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ድል ባደረጉበት የሃዋሳ ከተማው ጨዋታ ተሻሽሎ የተመለከትነው የቡድኑ ማጥቃት ግን ዳግም በወልቂጤው ጨዋታ የቀደሙት ችግሮች አገርሽተውበት ተመልክተናል። ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የተመለከትናቸው መቻሎች ይህን ክፍተት በዘላቂነት መቅረፍ ካልቻሉ ድሎችን በተከታታይነት የማስመዝገባቸው ነገር መሳካቱ እጅግ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአራት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን መቻሎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ በአንፃሩ የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሀል ዳኝነት ፣ ተከተል በቀለ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ ሊጉ በማደግ ሰብስቤ ጥላዬ በረዳትነት ፣ ተፈሪ አለባቸው በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል። እንዲሁም ዘመኑ ሲሳይነው በአዲሱ ምደባ የመቀየርያ ቦርድ የሚያዘጋጅ ይሆናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀድያ ሆሳዕና

የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ድል የተራቡትን ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን በእንቅስቃሴ ረገድ እየተቀዛቀዙ ከሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች ያገናኛል።

አሁንም የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድላቸውን ፍለጋ ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሙሉ ሦስት ነጥብ ካሳኩ 8 ጨዋታዎች ተቆጥረዋል ፤ በ7 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ አሁንም የብስለት ችግር እየታየበት ይገኛል።

በሁለቱም የሜዳ ፅንፎች ውስንነቶች ያሉበት ቡድኑ ከፍተኛ የልምድ እጥረት ያለበት ይመስላል። በመከላከሉ በተደጋጋሚ ኤሌክትሪኮች እያስተናገዷቸው የሚገኙ ጎሎች መቀረፍ የሚችሉ የነበሩ ሲሆን በተቃራኒም በማጥቃቱ የሚፈጥሯቸውን የግብ ዕድሎችን በስልነት የመጨረስ ችግር ቡድኑን ወደኃላ እየጎተተው ይገኛል።አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ወደ ገበያ የመውጣታቸው ነገር የሚቀር ባይመስልም አስቀድሞ የመጀመሪያውን ዙር በጥሩ ውጤት ለመጨረስ ቀጣዩቹ ሦስት ጨዋታዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው።

ለነገው ጨዋታ በኤሌክትሪኮች በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት አላዛር ሽመልስ እና ልደቱ ለማ ያገገሙ ቢሆንም የመስመር አማካዩ አላዛር ግን በነገው ጨዋታ አይሰለፍም።

ጥሩ የመጀመሪያ ዙር እያሳለፉ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከመሪዎቹ በቅርብ ርቀት በ19 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ነገርግን በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች የነበራቸው የሜዳ ላይ ብቃት እምብዛም አመርቂ አልሆነላቸውም። ለአብነትም በመጨረሻ ጨዋታቸው ከአዳማው ጨዋታ በግብ ጠባቂያቸው የግል ብቃት አንድ ነጥብ ይዘው ቢወጡም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር።

ጠበብ ባለ ስብስብ ውድድር ዘመኑን የጀመሩት ሆሳዕናዎች የተጫዋቾች ጉዳት እና ቅጣት በጨዋታዎች የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው ወስደው እንዳይጫወቱ ፈተና የሆነባቸው ቢመስልም የውድድር ዘመኑን ሲጀምሩ ከነበረው ግምት አንፃር ግን የተሻለ ጉዞ ላይ ይገኛሉ።

ሀዲያዎች በነገው ጨዋታ ባዬ ገዛኸኝ በቅጣት ቤዛ መድህን ደግሞ በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን መለሰ ሚሻሞ እና እንዳለ ደባልቄ ግን ከጉዳት ይመለሳሉ።

የምሽቱን መርሃግብር ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው መለሰ ንጉሴ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት ሲመራ ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና አማን ሞላ ረዳቶች ፣ ኤፍሬም ደበሌ በአራተኛ ዳኝነት በጋራ ሲመሩ ፣ ኤልያስ መኮንን የመቀየሪያ ቦርድ የሚያስተካክል ተጨማሪ ዳኛ ሆኗል።