የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ፣ ንፋስ ስልክ እና መቻል ወሳኝ ነጥብ አግኝተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተጀምረው መቻል ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ድል ሲያገኝ ድሬዳዋ እና ንፋስ ስልክም ወሳኝ ነጥብ ከተጋጣሚዎቻቸው ላይ አግኝተዋል።

ጠንከር ባለ ፀሀያማ የአየር ሁኔታ የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ 4 ሰዓት ሲል ተጀምሯል። ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አብዛኞቹ ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ፍትጊያዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተመሳሳይ መልክ የነበረውን ረጃጅም ኳሶች ያስመለከተን ነበር። ጨዋታው 4ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የቦሌ ተከላካዮች ስህተት አግዟት ስራ ይርዳው የምስራቁን ቡድን መሪ አድርጋለች። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በይበልጥ አቻ ለመሆን ከመስመር በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት መጣር የያዙት ቦሌዎች ከ11 ደቂቃ ቆይታ በኋላ በስንታየሁ ሒርኮ ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ጨዋታው ለ25 ደቂቃዎች የመቀዛቀዝ ቅርፅ የነበረው ቢመስልም 31ኛ ደቂቃ ላይ ቤዛዊት ንጉሴ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ላይ አክርራ የመታችው ኳስ የግብ ጠባቁዋ ትብቃ ፈንቴ ስህተት ተጨምሮበት ከመረብ ላይ አርፋ ድሬዳዋ 2ለ1 ሆኗል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የቦሌ ክፍለ ከተማዎች የሙከራ ብልጫን ያሳየን ቢሆንም የሚያገኙትን ኳስ ተጠቅመው የድሬዳዋን ተከላካይ አልፎ ግብ ለማስቆጠር ሳያድላቸው ጨዋታው 2ለ1 በእንስቶ ብርቱካናማዎቹ አሸናፊነት ተደምድሟል።

የሳምንቱ ሁለተኛ በሆነው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ሳይጠበቅ ተደጋጋሚ ሽንፈትን ሲያስተናግድ በነበረው ንፋስ ስልክ የበላይነት ተጠናቋል። ቡድኑ የአሰልጣኝ ዮናስ ወርቁን ረዳት የነበረውን ተስፋዬ መስፍን እና ቡድን መሪው ታደሰ መላኩ ከኃላፊነት በማንሳት በግብ ጠባቂ አሰልጣኙ መንግስቱ እየተመራ የዓመቱ ሁለተኛ ሙሉ ነጥቡን ወደ ካዝናው አስገብቷል። አዲስ አበባ ከተማ በእንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም የተከላካይ ክፍላቸው የአደራደር ስህተት ለንፋስ ስልክ አጥቂዎች እጅጉን አመቺ ሆኖ ቀርቧል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ 45ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በሬዱ በቀለ ንፋስ ስልክን መሪ አድርጋለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ አሁንም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ብልጫን ወስደው ቢታዩም የኋላ መስመራቸው ስህተት ቀጥሎ መቅደስ ታፈሰ ከረጅም ርቀት የግብ ጠባቂዋ በአንቺአየው ደመላሽ ስህተት ታክሎበት ንፋስ ስልክን ወደ 2ለ0 አሸጋግራለች። 81ኛ ደቂቃ ላይ አለም ባይቻ ሦስተኛውን ጎል ለንፋስ ስልክ ከመረብ ካገናኘች በኋላ በይበልጥ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ተደጋጋሚ ዕድልን የፈጠሩት አዲስ አበባ ከተማዎች መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊገባደድ ሲል በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በአማካዩዋ ኪፊያ አብዱራህማን ሁለት ጎሎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢሞክሩም ፍልሚያው በመጨረሻም በንፋስ ስልክ 3ለ2 ድል አድራጊነት ተፈፅሟል።

የቀኑ ማሳረጊያ በሆነው የመቻል እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክር አስመልክቶን በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ማለትም አራተኛ ደቂቃ ላይ እፀገነት ግርማ ከሳጥን ውጪ ባስቆጠረችው ግብ መቻሎች መሪ መሆን የቻሉ ቢሆንም በቀሩት ደቂቃዎች በአዳማ እጅጉን ተፈትነው በመጨረሻም በጊዜ ያገኙትን አንድ ጎል አስጠብቀው አሸንፈው ወጥተዋል።