አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በለገጣፎ አይቀጥሉም

ከሰሞኑ ለገጣፎ የለገዳዲን ለማሰልጠን ድሬዳዋ ተገኝተው የነበሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ላይመለሱ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎን እያደረገ የሚገኘው ለገጣፎ የለገዳዲ ከሳምንት በፊት የክለቡ ሦስት ረዳት አሰልጣኞችን ከኃላፊነት በማንሳት እና በዋና አሰልጣኝነት ይሰራ የበረውን አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመን ረዳት በማድረግ አሸናፊ በቀለን የክለቡ ቦርድ በዋና አሰልጣኝነት መሾሙ ይታወሳል።

አሰልጣኙ ይህንን ተከትሎ ምክትል አሰልጣኝ ኢያሱ መርሐፅድቅን (ዶ/ር) በመያዝ ወደ ድሬዳዋ መጥተው ክለቡ በ12ኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 ሲለያይ በስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉ እና በልምምድ ወቅትም ከቡድኑ ጋር ያለፉትን ጥቂት ቀናት የቆዩ ቢሆንም ከትናንት በስትያ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። አሰልጣኙ የሄዱበትን ምክንያት አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዝርዝር ነገሮችን ከመናገር ተቆጥበው እንደማይመለሱ ግን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።