መረጃዎች | 48ኛ የጨዋታ ቀን

በነገው ዕለት የሚደረጉ ሁለት የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ፋሲል ከነማ ከወልቂጤ ከተማ

 7ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እንዲሁም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አምስት ነጥቦችን የጣሉት ወልቂጤ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ነገ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ትግል ትኩረት እንደሚስብ ቀድሞ መናገር ይቻላል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በወጥነት ወጥ ብቃት ማሳየት ያልቻሉት ፋሲል ከነማዎች በስብስባቸው ውስጥ ከፍተኛ የተነሳሽነት ችግር ያለ ይመስላል። ቡድኑ ማሸነፍ ባልቻለባቸው ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ ይህ ችግር በግልፅ ሲታይ የነበረ ሲሆን በዋናነት ደግሞ ከወገብ በላይ ያለው የማጥቃት አጨዋወት መዳከሙ ዋጋ እንዲከፍል እያደረገው ይገኛል። ቡድኑ ዓምና የሊጉ ሁለተኛ ብዙ ግብ ያስቆጠረ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ግብ ተጋጣሚ መረብ ላይ ማሳረፍ አልቻለም።

ሊጉን በተከታታይ ድል የጀመረው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻለም። እርግጥ ቡድኑ ጨዋታዎችን በአዎንታዊ መንገድ ቢቀርብም አጨራረሱ ግን እየሰመረለት አይገኝም። በተለይ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ በዋናነት ደግሞ በመጨረሻ ደቂቃዎች ያለው የጨዋታ ቁጥጥር እና የትኩረት ጉዳይ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። ለዚህ ማሳያ ቡድኑ በ12 ጨዋታዎች ካስተናገዳቸው 14 ጎሎች 57 % በሁለተኛው አጋማሽ የተገኙ ሲሆን 50% ደግሞ ከ75 ደቂቃ በኋላ የተቆጠሩበት ናቸው።

በዚህ ጨዋታ ላይ ፋሲል ከነማ ከሀብታሙ ተከስተ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ፋሪስ አላዊ እና ውሀብ አዳምስን በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ሲመራ ባደታ ገብሬ እና ፍቅሬ ወጋየሁ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አራት ጊዜያት ተገናኝተው ሦስቱን ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ 1ለ0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ዓምና የተደረገውን የመጨረሻ ግንኙነት ደግሞ ወልቂጤ ፋሲል ላይ የመጀመሪያ ድሉን 2ለ1 በሆነ ውጤት አፅፏል።

ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ መድን

በዘጠኝ ነጥቦች እና አስር ደረጃዎች ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና ነገ ምሽት የሚያደርጉት ፍልሚያ እንደ ቀኑ ጨዋታ የብዙዎችን ቀልብ እንደሚገዛ ይገመታል።

ከውጤት ማጣት ጋር በተገናኘ ክረምት ላይ ከተሾሙት አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና ከአንድ ሳምንት እረፍት በኋላ በምክትል አሠልጣኙ ዮሴፍ እየተመራ ጨዋታውን ይጀምራል። አዲስ ግንባታ ላይ የሚገኘው ስብስቡ በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች የውህደት ክፍተት ያለበት ሲሆን በተለይ በመከላከሉ ረገድ ያለው ችግር የራስ ምታት ሆኖበታል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎችም ግቡን መጠበቅ ሳይችል 11 ግቦችን አስተናግዷል። ይህንን የኋላ ውቅር ሽንቁር ለመድፈን የተለያዩ ጥምረቶች ቢሞከሩም ውጥኑ ሊሰምር አልቻለም። የሆነው ሆኖ ግን በአሠልጣኝ ለውጦች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚታየው መነቃቃት ቡናም ቤት ነገ ከተከሰተ በጥሩ ቁመና ላይ ለሚገኘው መድን ፈተና ሊሆን ይችላል።

ከብዙዎች ግምት ባፈነገጠ የውጤት ፌሽታ ጉዞ ላይ የሚገኘው የወቅቱ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሳይጠበቅ ምርጥ ቡድን እንደሆነ እያሳየ ነው። ከአስከፊው የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሽንፈት ወዲያው በማገገም ከጨዋታ ጨዋታ ራሱን እያጠናከረ የመጣው ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በመጠኑ ወጥ ነገር ማሳየት ቢሳነውም በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መገኘቱ የራስ መተማመኑን የሚያሳድ ነው። መድን ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ተመሳሳይ ተጫዋቾችን አዘውትሮ የሚጠቀም ነው። ከዚህ ስብስብ የአማካይ መስመሩ ውቅር ደግሞ ጨዋታን ለመቆጣጠር ወሳኝ ሚናን ሲወጣ በተደጋጋሚ ይታያል። በነገውም ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው ቡና ጋር የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ለመውሰድ የሚያደርጉት የመሐል ሜዳ ፍትጊያ የሚጠበቅ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና አማኑኤል ዮሐንስ እና አስራት ቱንጆ ከጉዳት ቢያገግሙለትም ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው ግን አጠራጣሪ መሆኑ ተመላክቷል። በኢትዮጵያ መድኖች በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ከራቀው ሳሙኤል ዮሀንስ በተጨማሪ ሀብታሙ ሸዋለምም የነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያመልጠው ይሆናል።

ይህን ጨዋታ ደግሞ ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት አማን ሞላ እና አያሌው ማንደፍሮ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ዳንኤል ግርማይ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ሁለቱ ቡድኖች 25 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 11 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 5 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። ኢትዮጵያ ቡና 42 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ 28 ጎሎች በስሙ አሉት።