ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ13ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ13ኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች መነሻነት የሳምንቱን ምርጥ 11 እና አሰልጣኝ መርጠናል።

አሰላለፍ – 4-3-3

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

ሰባት ግብ ጠባቂዎች መረባቸውን ባላስደፈሩበት በዚህ ሳምንት ጥሩ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾች ተበራክተዋል። ሆኖም አቡበከር በሁለተኛው አጋማሽ ያዳናቸው የኢትዮጵያ ቡና ሙከራዎች መድን ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ ከማድረጋቸው አኳያ የሳምንቱ ምርጥ አድርገነዋል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጊዮርጊስ ለገጣፎን ሲረታ የቡድኑ የቀኝ ክፍል በተጋጣሚው ላይ ለነበረው ብልጫ የሄኖክ ቀጥተኛ ሩጫዎች ወሳኝ ነበሩ። በጨዋታው በክፍት እንቅስቃሴ ሁለት አደገኛ የግብ አጋጣሚዎችን የፈጠረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ የፍሪምፖንግ ሜንሱን ጎል ከቆመ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

ፍፁም ግርማ – ወልቂጤ ከተማ

ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ከተጫወተበት 6ኛው ሳምንት ጀምሮ ከሜዳ ያልጠፋው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ፍፁም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታ የመሀል ተከላካይ ቦታን ይዞ ጥሩ ብቃት ሲያሳይ ነበር። ተጫዋቹ በፈታኙ የፋሲል ጨዋታ አዲሱን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት የተጋጣሚን የአየር እና መሬት ጥቃት እያመከነ የቡድኑ ግብ እንዳይደፈር የበኩሉን ተወጥቷል።

ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

የዋልያዎቹ ስብስብ አካል የሆነው የአዳማ ከተማው የመሀል ደጀን ከጉዳት መልስ በመልካም አቋሙ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት ከድሬዳዋ በተገናኙበት ጨዋታ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶችም ሆነ የጥቃት አቅጣጫዎችን ቀደሞ በመለየት የተከላካይ መስመሩን የመራበት መንገድ ቡድኑ ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አስተዋፅዖ ነበረው።

መሀሪ መና – ሲዳማ ቡና

3-3 በተጠናቀቀው የሳምንቱ አስገራሚ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ አቻ እንዲሆን መሀሪ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ይልካቸው የነበሩ ኳሶች እጅግ ወሳኝ ነበሩ። በዚህም ተጨዋቹ ለመጀመሪያው ጎል እንቅስቃሴ መነሻ መሆን ሲችል ሦስተኛውን የቡልቻ ሹራን ግብ ደግሞ በቀጥታ አመቻችቶ አቀብሏል።


አማካዮች

ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በለገጣፎው ጨዋታ ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ሀይደር ግብ ማስቆጠር ብቻ ነበር የቀረው። በተደጋጋሚ ዘግይቶ ሳጥን ውስጥ በመግባት እና ሁነኛ ቦታ ላይ በመገኘት አደገኛ ሙከራዎችን ያደረገው አማካዩ ቸርነት ጉግሳ ላስቆጠራት ግብ ከዚሁ ቦታ ላይ የመጨረሻውን ኳስ በልዩ ሁኔታ ማቀበል ችሏል።

መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ

ባለ ብዙ ልምዱ አማካይ በአዳማ ከተማ መለያ በታታሪነት መንቀሳቀሱን ቀጥሏል። ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ መሀል ሜዳ ላይ የነበረውን ፍልሚያ በአስፈላጊ ጊዜያት ላይ ወደ ራሱ ማድረግ እንዲችል እስከተጋጣሚ ሳጥን ድረስ ይዘልቅ የነበረው የመስዑድ የቅብብል ክዋኔ አስፈላጊው ነበር።

ፍፁም ዓለሙ – መቻል

ፍፁም ባለፉት ዓመታት ያሳየውን አቋም በመቻል መለያ የደገመበትን የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል። ቡድኑ ባህር ዳርን ሲረታ ኳስ በመንዳት በተጋጣሚ የግብ ክልል ዙሪያ አደጋ ሲፈጥር ይታይ የነበረው ተጫዋቹ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሁለቱን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አጥቂዎች

ኪቲካ ጀማ – ኢትዮጵያ መድን

የሊጉ ትኩረት ማረፊያ የሆነው ኪቲካ በዚህ ሳምንት ግብ ባያስቆጥርም ለብቸኛዋ የፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት ነበር። ተጫዋቹ የቡድኑን የግራ መስመር ጥቃት በመምራት የኢትዮጵያ ቡናን የቀኝ ተከላካይ ክፍል ደጋግሞ መረበሽ የቻለበትን እንቅስቃሴ አድርጓል።

ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና

ይገዙ ቦጋለ ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ ሦስት ጎል በማስቆጠር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ለቡድኑ መነሳሳት ከፍ ያለ ሚና ነበረው። የቡድኑን ስሜት በማነሳሳት በተደጋጋሚ ጥቃቶች ውስጥ ድርሻ የነበረው ይገዙ አንድ አደገኛ ዕድል ሲፈጥር ሁለት ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል።

ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቶጓዊው የፈረሰኞቹ የፊት መስመር ተመራጭ አጥቂ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መምራቱን ቀጥሏል። ቡድኑ ለገጣፎን ሲረታ ሁለት ግቦችን በግንባሩ ያስቆጠረው አጎሮ በእንቅስቃሴ ለተከላካዮች አስቸጋሪ ሆኖ በዋለበት ጨዋታ በዘጠኝ ሰኮንዶች ውስጥ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ጭምር ታሪክ ሰርቷል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

በመቻል ቆይታቸው ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፉት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ነገሮች የተስተካከሉላቸው ይመስላል። ከባድ በነበረው የባህር ዳር ጨዋታ ቡድናቸው በተለይም በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ አስፈሪነትን እንዲላበስ በሚያደርግ የጨዋታ ዕቅድ በመጀመር እና ስኬታማ ቅያሪዎችን በማድረግ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ አድርገዋል።

ተጠባባቂዎች

ሮበርት ኦዶንካራ – ወልቂጤ ከተማ
ሀቢብ መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን
ሳለአምላክ ተገኘ – ባህር ዳር ከተማ
በኃይሉ ግርማ – መቻል
ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቢኒያም አይተን – አዳማ ከተማ
እስራኤል እሸቱ – መቻል
አህመድ ሁሴን – አርባምንጭ ከተማ