የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክ በሰፊ ጎል አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻቸው ላይ በርከት ያሉ ጎሎችን አስቆጥረው ድልን ሲያስመዘግቡ መቻል እና ቦሌ ነጥብ ተጋርተዋል።

በሀዋሳ እየተደረገ የሚገኘው የሊጉ ጨዋታ 8ኛ ሳምንቱ ላይ ደርሶ ረፋድ 4 ሰዓት ሲል ቀዳሚው ጨዋታን አስተናግዷል። ለዕይታ ማራኪ በነበረው እና ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የመቻል እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በመጨረሻም በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ላይ ኳስን በመቆጣጠር በተጋጣሚያቸው መቻሎች የጨዋታ ብልጫን ቢያሳዩም ካስቆጠሯት ግብ ውጪ በቀላሉ የቦሌን የተከላካይ ክፍል በማለፍ ግብን ለማግኘት በእጅጉ ተቸግረው ተስተውሏል። ወጥነት ባለው ጥሩ ቅብብል መነሻውን ከማዕድን ሳዕሉ ካደረገ ኳስ 6ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ኳስ እና መረብን አገናኝታ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ አመዛኙን የጨዋታ ጊዜ በማሳለፋቸው ተጨማሪ ግብን መመልከት ሳንችል አጋማሹ ተጠናቋል።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ሲቀጥል ከመጀመሪያው አጋማሽ ክፍተቶቻቸው በሚገባ ታርመው ወደ ሜዳ የተመለሱት የአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻው ቡድን ቦሌ ክፍለ ከተማ በመቻል ላይ የበላይነቱን መውሰድ ችሏል። መቻሎች ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ አራት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ በመልሶ ማጥቃት ሴናፍ ዋቁማ ለቡድኗንም ሆነ ለራሷ ሁለተኛ ግብን ከመረብ ከዋሀደች በኋላ የጨዋታው የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ወደ ቦሌ አመዝኗል። ወደ ጨዋታ ለመመለስ ኳስን በመቆጣጠር ወደ መስመር አመዝነው ጨዋታቸውን የቀጠሉት ቦሌዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በይበልጥ ባደረጉት ትጋት 72ኛ ደቂቃ ላይ ንግስት በቀለ በጥሩ ቅልጥፍና ያመቻችላትን ኳስ ከሳጥን ውጪ ስንታየሁ ሒርኮ አክርራ መትታ ጎል አስቆጥራለች። መቻሎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሴናፍ ዋቁማን የትኩረት ማዕከል አድርገው ቢጫወቱም ግብ ጠባቂዋ ትብቃ ፈንቴ መረቧን አላስደፍር በማለት የሚገርም ብቃቷን ስታሳይ አስተውለናል። ይሁን እንጂ በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት ቦሌዎች ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ 84ኛ ደቂቃ ላይ በድንቅ አጨራረስ ንግስት በቀለ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 2-2 በሆነ የአቻ ውጤት ፍፃሜን አግኝቷል።

8 ሰዓት ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ፀሀያማ በነበረው የሀዋሳ አየር ታጅቦ ተጀምሯል። የቅዱስ ጊዮርጊስ የእንቅስቃሴም ሆነ የሙከራ ብልጫ የበላይነትን የመጀመሪያው አጋማሽ ያስመለከተን ሁነትን ታዝበናል። መሀል ሜዳ ላይ መነሻቸውን አድርገው በሁለቱም ኮሪደሮች ለማጥቃት ተጭነው መጫወት የጀመሩት ጊዮርጊሶች ጨዋታው በጀመረ ሦስተኛ ደቂቃ ላይ ከዚህ የጨዋታ መነሻ ዓይናለም ዓለማየሁ ከግብ ጋር ተገናኝታ ማርታ በቀለ ያዳነችባት አስገራሚው የቡድኑ አጋጣሚ ነበር። ከወትሮ አጨዋወታቸው ረጃጅም ኳስ ላይ ያዘወተሩት ኤሌክትሪኮች አብዛኛውን ደቂቃ ኳስን በመያዝ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ቢጥሩም የሚቆራረጡ በመሆናቸው ልዩነት ለመፍጠር አላስቻላቸውም። በአንፃሩ በአጋማሹ በሶፋኒት ተፈራ እና ዓይናለም ዓለማየሁ አማካኝነት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዕድሎችን ቢያገኙም ኳስን ከመረብ ማገናኘት ባለ መቻላቸው አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ በመጀመሪያው አርባ አምስት ደካማ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራቸው ኤሌክትሪኮች በእጅጉ ተሻሽለው በመቅረብ ግቦችን ወደ ማስቆጠሩ ተዘዋውረዋል። 65ኛ ደቂቃ ላይ መሰሉ አበራ ከርቀት አክርራ መታ የግቡ የላይኛው ብረት ሲመልስው ትዕግስት ያደታ ደርሷት በግንባር ገጭታ ከመረብ አዋህዳለች። ጎሉን ካገኙ በኋላ በይበልጥ ጥቃት መሰንዘርን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች በሰላማዊት ጎሳዬ ሁለተኛ ግብን ሲያስቆጥሩ ከሦስት ደቂቃ ቆይታ መልስ ሰላማዊት አቀብላ ሰብለወንጌል ወዳጆ በጥሩ አጨራረስ ጎል አድርጋለች። መደበኛው የጨዋታው ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ላይ ተቀይራ ከገባች ሜዳ 40 ሰከንድ ብቻ የሞላት ዓይናለም አሳምነው አራተኛ ጎል አክላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የ4-0 አሸናፊ ሆኗል።

የዕለቱ የመጨረሻ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ንግድ ባንክ ግማሽ ደርዘን ጎል ተጋጣሚው ላይ አሳርፎ አሸንፏል። ጨዋታው አጀማመሩ በተለይ ለአስር ደቂቃዎች ያህል የተመጣጠነን እንቅስቃሴ መመልከት ያስቻለን ቢሆንም የኋላ ኋላ የጨዋታው የኃይል ሚዛን ወደ ንግድ ባንክ አጋድሏል። 13ኛው ደቂቃ በንፋስ ስልክ የተከላካዮች ስህተት መነሻነት አረጋሽ ካልሳ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጋለች። 34ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት ማራኪ የሆነች ጎል አሳርፋ የባንክን የጎል መጠን ከፍ አድርጋለች። ተደጋጋሚ የሆኑ ጥቃቶችን መሰንዘር የቀጠሉት ባንኮች 43ኛ ደቂቃ የንፋስ ስልክ ተከላካይ አሶሬ ሀዬሶ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ግብ 3-0 በሆነ ውጤት አጋማሹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ጫናን ወደ ማሳደሩ ያመዘነ ተሳትፎን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በሎዛ አበራ የ52ኛ ፣ የ65ኛ እና 68ኛ ጎሎች 6ለ0 በሆነ ድል በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን አሸናፊነት ተደምድሟል።